ዛሬም የእግዚአብሄር ጥያቄዎች (ክፍል ሁለት)
ባለፈው እትማችን ዛሬም የእግዚአብሄር ጥያቄዎች በሚል ርዕስ ስር፡ 1. ወዴት ነህ? 2. ለምን ፊትህ ጠቆረ? 3. ወንድምህ ወዴት ነው? የሚሉትን እግዚአብሄራዊ ጥያቄዎችን በዝርዝር አይተን ነበር። ዛሬ ከዚያ የሚቀጥሉትን አምላካዊ ጥያቄዎች ለማየት እንሞክራለን። ይህ ማለት የእግዚአብሄር ጥያቄዎች አሁን በፅሁፋችን ላይ ያሰፈርናቸው ብቻ ናቸው ማለት አይደለም። በእያንዳንዳችን መንፈስና አይምሮ (ህሊና) ላይ እለት እለት በምናደርጋቸውና በምንሆናቸው ነገሮች ላይ በሚገባን መንገድ እግዚአብሄር እኛን መጠየቁ አይቀሬ ነው።
4.ስምህ ማነው? ዘፍ32፥25-28
በዚህ የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል በተለያዩ ሰባኪዎች እና ፀሀፊዎች ብዙ ስለተባለለት ይህንን የመፅሀፍ ክፍል የማያውቀው ሰው አለ ብዪ አልገምትም፤ ባንሰብከውም ቢያንስ አንብበነዋል። እንግዲህ ይህ “ስምህ ማነው” ጥያቄ ለአባታችን ለያዕቆብ የቀረበ ጥያቄ ነው። እግዚአብሄር የትውልድ አባት፣ የነገዶች ሁሉ አባት፣ የአንድ አገር መጠሪያ ሊያደርገው ስላሰበ፣ በድሮ ማንነቱ ወይ በያዕቆብነቱ (በአታላይነቱ) እንዲቀጥል ስላልፈለገ፣ ታሪኩንም ስሙንም መቀየር ስለፈለገ፣ የማነው ስምህ ጥያቄ የመጀመሪያው የለውጥ ምዕራፍ ነበር። እስኪ በመጀመሪያ ስለ ያዕቆብ ትንሽ እንይ። ያዕቆብ ማነው? ያዕቆብ በረከትን በአቋራጭ ለማግኘት ሲፈልግ ስሙን ይቀይራል፤ ያዕቆብ ኤሳው ይሆናል፣ ያዕቆብ መሆን ባይችልም ማስመሰልና መምሰል ይሞክራል፤ ፈዘዝ ያሉትን እንደ አባቱ ይስሐቅ ያሉትን አታሎ ያልሆነውን ነኝ ብሎ ለበረከት መክፈል ያለበትን ዋጋ ይከፍላል፤ ያዕቆብ ውስጡን ብቻ አይደለም ውጭውንም በሜካፕ ራሱን ይቀይራል። ያዕቆብ የሚጣፍጥ የምስር ወጥ በመስራት በኩርናን በምስር ወጥ ይለውጣል። በአጠቃላይ የያዕቆብ ልምምድ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ- የሁሉ ነገር ባለቤት እና ተሽሎ መታየት የሚፈልግ ሰው ነው። ያዕቆብ ብልጣ ብልጥ ሰው ነው፤ ያዕቆብ ሸሽቶ ወደ አጎቱ ጋር ሄዶም ያንኑ ልምምዱን ቢቀጥልም፥ አጎቱ ላባ ከሱ የባሰ ብልጥ ነበርና ለአንድ ሴት ለሀያ አንድ ዓመት ጉልበቱን በዘበዘው። በአንድ ወቅት በዚህ ክፍል ላይ ስለ ላባ ስንነጋገር ላባና የዚህ ሀገር የክሬዲት ሲስተም በጣም ተመሳሳይነት እንዳለው ለማየት ሞክረን ነበር። ባህር ተሻግረን ወደዚህ አገር ስንመጣ አበዳሪዎች በነፃ የሚሰጡን ያክል ይወተውቱንና ሲስተሙ ውስጥ ከገባንላቸው በኋላ መልኩን እየቀያየረ ለዘመናት እንደሚገዙን ሁሉ ላባም ደሞዙን እየለዋወጠ ለዘመናት ገዛው። በአይኑ ፊት ያማረችውን ራሄልን ብሎ ማንም ሳያስገድደው ላባ ለራሄል ሰባት ዓመት ተገዛልኝ ሳይለው ፈቃዱን አሳልፎ በመስጠት በፈቃዱ በር ከፍቶ መዝጊያው ቸገረው። በዚህ አጋጣሚ ኑሮዪ ይበቃኛል ብለን ልንወጣው ከማንችለው አዘቅት ውስጥ እንዳንገባ በመጠን እንኑር። አቅማችንን አውቀን ከፉክክር የፀዳ፣ እንደቤታችን እንጂ እንደ ጎረቤታችን ለማደር አንሞክር እያልኩ ወደ ተነሳሁበት ሀሳብ ልመለስ።
ታድያ ያዕቆብ የብዙ መንጋ ባለቤት፣ የብዙ ልጆች አባት፣ የብዙ ሚስቶች ባል ሆኖም በአቋራጭ የመጣ በረከት ውስጥ ውስጡን አልሞላ ብሎት ዛሬም የበረከት ጥያቄ ልቡን ሞልቶት እስኪነጋ ይታገለው ለነበረው ሰው የበረከት ጥያቄ ሲያቀርብ እናያለን። ዛሬም ይህ የስምህ ማነው ጥያቄ ለአባታችን ለያዕቆብ ብቻ ሳይሆን ለዘመኑ ያዕቆቦች ለእኛም ነው። ዛሬ ስማችን ማነው? ለእያንዳችን ይህ ጥያቄ አለልን። ያዕቆብ የተለያየ ገፀ ባህሪያት ተላብሶ ሲጫወት እንዳየነው እንዲሁ እኛም ብዙዎቻችን ብዙ ስሞች አሉን። ቤተሰባችን ያወጣልን ስም አለ፣ እኛ ደግሞ እንድንጠራበት የምንፈልገው መጠሪያ ስም አለን። ዛሬ በብዙ ስም መጠራታችን ተስማምቶን ከሆነ ሁሌ የድንጋጤና የሰቆቃ ህይወት እንኖራለን። ዛሬ ግን ለስምህ ማነው ጥያቄ ትክክለኛ መልስ የምንሰጥ ከሆነ ለጊዜው የጭናችን ሹልዳ ተነክቶ ቢያመንም ቆስለን አንቀርም፤ ድነን እንቀራለን፣ ስማችን ከሌባው ወደ ታማኙ፣ ከውሸታም ወደ እውነተኛ፣ ከአመንዛሪ ወደ ቅዱስ፣ ከቀናተኛ ወደ ተደሳችነት ይቀየራል። ከዚያ በፊት ያዕቆብ ኤሳው ነኝ ሲል በቆየበት በዚያው አንደበቱ እኔ ያዕቆብ ነኝ ሲል ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ያዕቆብ አይባል እስራኤል እንጂ ተባለ።
አንድ እውነት ልንገራችሁ ለአታላይነታችን ንስሀ ገብተን ትክክለኛ ማንነታችንን ለእግዚአብሄር እንንገረው። ትውልድ በእኛ እንዲባረክ ከፈለግን በሁለት ማሊያ መጫወት አብቅተን የሰፈር ማንነታችንንና የአደባባይ ማንነታችንን ማስታረቅ የምንችለው ትክክለኛ ማንነታችንን በእግዚአብሄር ፊት መግለጥ ስንችል ነው።
አሁን ሊባርከን በደጅ ያለው እንደ ይስሐቅ አይኑ የደከሙና ያረጀ እንዲሁም ተርቦ የሚታለል አይደለም። ለዘመናት እርጅና አያውቀውም፤ ዳስሶ እና ገምቶ የሚባርክ ሳይሆን ዘልቆ ልብን ያያል፤ እስከ ዛሬ ብልጣብልጥ ሆነን ብዙ ሰዎችን አታለን ተሳክቶልን ይሆናል፣ በረከት የሚመስል ግን ያልሆነ ስንወጣና ስንገባ ህሊናችንን እየወቀሰን ከህሊናችን ወቀሳ ለማምለጥ በተለያየ ነገር ውስጥ ራሳችንን የደበቅን፣ የትም አናመልጥም! ህሊና የመንፈሳችን (አካል) ነው። ህሊና በአልኮል አይደነዝዝም፤ በዝማሬና በመንፈሳዊ ስርዓቶችም ዝም አይልም፤ ትክክለኛ ምላሽ እስክንሰጠው ድረስ አንዳንዶቻችን የምንጠቀምባቸው እቃዎች፣ የምናጌጥባቸው ጌጣጌጦች፣ የምንነዳቸው መኪናዎች ሳይቀሩ ስንወጣና ስንገባ ይጮሁብናል፥ አለቦታችን ነው የመጣነው፣ ተሰርቀን ነው፣ በግፍ ነው እያሉ ያስተጋባሉ። ምናልባት በውጭ ለሚያየን ሰው ሰላም ያለን እንመስል ይሆናል፣ ይህ ግን ለሰላም ንጉስ የተገለጠ ነው። አሁንም በእንደዚህ ህይወት ልምምድ ውስጥ ያለን ለትውልዳችን እርግማን ለቤተሰባችን ካንሰር ጥለን አንለፍ! ከእኛ ወደ ትውልዳችን እንዳያልፍ አሁን ንሰሀ እንግባ፣ እንመለስ ዛሬም ደሙ ትኩስ ነው። ሊያነጻን የታመነ ነው።
ወገኖቼ ምናልባት ጥሩ አስራት በማውጣት፣ ለድሆች በመስጠት፣ ስጦታን ለአገልጋዮች በመስጠት ዕረፍት ለማግኘት የምንሞክር ካለን ያ በፅድቅና በቅድስና እስካልመጣ ድረስ ምላሹ አደገኛ ነው (ሐዋ ስራ 5፥1)መንፈስ ቅዱስ ሰው አይደለም፣ አይታለልም። እናስተውል ያዕቆብ ትክክለኛ ስሙን ከተናገረ በኋላ እግዚአብሄር እንኳ የያዕቆብ አምላክ ተብሎ እንዲጠራ ፈቃደኛ ነበር። እስቲ ወገኖቼ አብረን ይህን ፀሎት አንፀልይ:
“እግዚአብሄር አባት ሆይ እስከ ዛሬ ድረስ ራሴን ሳታልል ቆይቻለሁ አሁን ግን በፊትህ ንሰሀ እገባለሁ፣ አንደበቴንና ልቤን በአንድ ቃል አስማማልኝ። እኔ ካንተ ጋር መስማማት እፈልጋለሁ። በደልና መተላለፌን በደምህ ደምስስልኝ፤ በትክክለኛ ማንነቴ እንድኖር እርዳኝ። ስሜን ቀይርልኝ! አሜን!”