አንደበት እሳት ነው!
ከግዮን ውብሸት
ላይን የሚማርክ ደን ጫካውን፣
መዓዛ ሽታው የሚያረካውን፣
ለጆሮ ሚጥም የወፎች ፉጨት፣
ንፁሁ አየር አቅልን የሚያስት፣
ወፍ አራዊቱ ሁሉም ባንድነት፣
ስብስብ ብለው የሚኖሩበት፣
አንዱ በሜዳ አንዱ በዛፍ ላ ይ፣
ሌላ ው ባየር ላ ይ በጠራው ሰማይ፣
ገሚሱ ደግሞ ሲል ብቅ ጥልቅ፣
እጅግ ባማረው ሰማያዊ ሀይቅ፣
በየተራራው በየሜዳው ላ ይ ፍጥረት ሲቦርቅ፣
በልዩነት ውስጥ የሚገለጠው፣
አቤት ሲያስቀና አንድነታቸው።
ታዲያ ይህንን የሚመስል፣
ማራኪ እና ደግ ባህል፣
እንዴት ሊወድም እንደሚችል፣
እስኪ ላውጋችሁ ስሙኝ በውል።
ከለታት አንድ ቀን አንድ ዝንጉ ወጣት፣
ጭንቀትና ሃሳብ ነፍሱን የሚንጣት፣
ወደ ጫካ ሄዶ እራሱን ሊያዝናና፣
ከዛፎቹ መሀል ትንሽ አረፈና፣
ህፃን ልጅ ሲያለቅስ በታላ ቅ ጩኸት፣
አባት ወይ እናቱ ጡጦ እንዲሰጡት፣
ይኼም ዝንጉ ወጣት ያው ዝንጉ ነውና፣
ከሲጋራ ፓኮው ጡጦ መዘዘና፣
ይመገምግ ጀመር ተደላ ደለና።
መግምጎ መግምጎ ያዋቂውን ጡጦ፣
ወርወር አደረጋት ቦታ ሳያይ መርጦ።
ያቺ የእሳት ፍም መች የዋዛ ሆና፣
ካንደኛው ወዳንዱ ትወረወርና፤
የዛፎቹን ቁመት ያበቦቹን ውበት፣
የወፎቹን ፉጨት ያናብስቱን ግሳት፣
የወንዞቹን ፍሰት የደኑንም ልማት፣
ቀስ ቀስ እያለች አቀጣጠለችው፣
የተረፈውንም ከዚያ አባረረችው፣
ያንን መሳይ ስፍራ፣
ጭው ያለ በረሃ ኦና አደረገችው።
ይኼም ወሬ ወጣ ተሰማ ለሁሉ፣
ጡጦ መሳይ ነገር፣
ደንን ያክል አገር፣
አጠፋ አወደመ ብለው ኡ ኡ አሉ።
ይኼ ክፉ ዜና ያስደነገጣቸው፣
የዕፅዋት አይነት ከነዘሮቻቸው፣
የችግሩን ጥልቀት ከስሩ መርምረው፣
መላ የሚሉትን አውጥተው አውርደው፣
ታደሙ ባንድ ላይ እንወያይ ብለው።
የስብሰባቸውን የውሳኔ ሃሣብ፣
አንድ ቀጥ ያለ ዛፍ ጀመረ ማነብነብ፥
“የተደቀነብን ችግር አሳስቧችሁ፣
የተሰው ዛፎች ደም አስቆጥቷችሁ፣
ጥሪውን በማክበር ወዲህ የመጣችሁ፣
ውድ ወገኖቼ እንደምን አላ ችሁ!!
“ከጥንት ካባቶች ዘመን አንስቶ፣
ተዘግቶ አያውቅም በራችን ከቶ።
የእረፍት ያለህ ብለው ሲመጡ፣
ብለን አናውቅም አይሆንም ውጡ።
ሊሸሸጉ እንኳን እኛን ሲቀርቡን፣
ዋሾቻችንን አልከለከልን።
ሲጠጋጉንም ምግብ ፍለጋ፣
የናቶች ጓዳ ከቶ አልተዘጋ።
ታዲያ እንደምላ ሽ ለውለታችን፣
ከበሬታና ፍቅር ሲገባን፣
ይኼው ተነስቷል አዳም ሊያጠፋን፣።
ስለዚህ እኛም ከዛሬ አንስተን፣
ከሌሎች ደኖች ስህተት ተምረን፣
እንጠብቃለን ዙሪያ ገባውን።
“ደስታ ከሆነ የሚፈለገው፣
እንዲህ አይነቱን አንከልክለው።
የጨነቀውም እረፍት የሚሻ፣
ይግባ ግድ የለም ይረፍ እንዳሻ።
ከኋላም ካለ የሚያሳድደው፣
ተውት ግድ የለም ዋሻው የሱ ነው።
መዓዛችንም ከሆነ ማርኮት፣
ይዝለቅ ወደ ውስጥ ምንም የለበት።
“ነገር ግን ብቻ ማንም ይሁን ማን፣
እንደው በእጁ ያቺ ጡጦውን፣
ይዞ ከሆነ ማስታገሻውን፣
እሱን እራሱን እንደማይጠቅመው፣
በመጀመሪያ ምክር ይሰጠው።
ያደገብኝ ነው በዋዛ አይለቀኝ፣
ከሆነ ደግሞ ብሎ የሚያመካኝ፣
እነ ባህር ዛፍ እነ ወይራ፣
ከነጤና አዳም አሪቲ ጋራ፣
ሱስኛውን ሰው በደምብ ያጥኑት፣
ውልቅ ብሎ እንዲወጣለት።
“መድሃኒቱና ምክሩ በሙላ ው፣
ግሳጼውና እንክብካቤው፣
ከአልመለሱት ወደ አይምሮው፣
ሁሉም የራሱን በር እየዘጋ፣
ሌትም ሆነ ቀን ሳይዘናጋ፣
ልዩ ክትትል እንዲያደርግበት፣
ለንዲህ አይነቱ የለም ምህረት።
ከቅጥር ውጭ ሆኖ እንኳን ድንገት፣
እሳቷን ወዲህ ቢወረውራት፣
ገና ስትነካን ላ ለመቃጠል፣
ድርቀቱን ትተን ረስረስ እንበል።
ቦታ አግኝቶ በእኛ መሀል፣
እንዳይበረታ የነፋሱ ሀይል፣
ነበልባሉንም እንዳያጋግል፣
በመሀላ ችን ያለውን ክፍተት፣
በመጠጋጋት እናጥብብበት!!”
ይኼን አጭር ወግ ላ ስተዋለው፣
ከተረት በላ ይ ፋይዳ አለው።
ልክ እንደጫካው ያማረበት፣
የተከበረ አገልግሎት፣
የተወደደ ቅዱስ ህብረት፣
ወሬ በሚሉት ክፉ እሳት፣
ማምራቱ አይቀርም ወደጥፋት።
የማያስተውል ዝንጉ ምላ ስ፣
የሚዘለዝል እንደ መቀስ፣
ያልተቀደሰ ተራ አንደበት፣
ሹክታው ሃሜት፣
ጩኸቱ ኩራት የሆነበት፣
ከመሃል ገብቶ እንዳያምሰን፣
እንዲህ አይነቱን አርቀን አይተን፣
ልናስተምረው ይገባል ቆርጠን፤
ልንገስፀው ይገባል ደፍረን።
አንደበት እሳት ነው የእሳት ነበልባል፣
የፍጥረትን ሁሉ ሩጫ ያቃጥላ ል።
አንደበት እሳት ነው ክፉ የእሳት ረመጥ፣
አርበኛውን ሁሉ ድንገት እጅ የሚያሰጥ።
የቅዱሳንን አቅም ሰባሪ፤
የለጋሱን ሰው እጆች አሳሪ፤
የየዋሁን ልብ ያረገ ጨካኝ፤
ያማረበትን ሁሉ አመንማኝ፤
ይቅር ባዩን ሰው ክፉ ቂመኛ፤
ቸር ሩህሩሁን ደግሞ ቀማኛ፤
እሹ ባይና እርግብግቡን ሰው፣
እምቢተኛና አባይ ያረገው፣
ከምንም በላይ ዝንጉ ምላ ስ ነው።
የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽ፤
ከተናገሩት ተሮጦ አይሸሽ፤
ነውና ጥንትም ያባቶች ተረት፣
ላፋችን ልጓም እናብጅለት።
ሰኔ 2001