ዛሬም የእግዚአብሄር ጥያቄዎች
እግዚአብሄር በዘመናት ሁሉ መካከል ለአገር፣ ለቤ/ክርስቲያን፣ ለግለሰብና ለትውልድ ጥያቄ አለው። የእግዚአብሄር ጥያቄዎች መልስ ይሻሉ፤ እግዚአብሄር መልስ የሌለውና የማናውቀውን ጥያቄ አይጠይቀንም። አንዳንዴ በገሀዱ አለም እንደምናየውም፣ እንደምንሰማውም አጥርቶ ካለመስማት ከጥያቄው ጋር ፈፅሞ አብሮ የማይሄድ መልስ እንመልሳለን፤ ወይም በግምት የመሰለንን እንመልሳለን፤ እንዳንዴም በህብረተሰባችን ዘንድ እንደ አዋቂ ከተቆጠርን አያውቅም ላለመባልና አላውቅም ላለማለት ነገሮችን እናወሳስባቸዋለን። ለጥያቄው የጥያቄ መልስ እንሰጣለን፤ ወይም ከሌሎች የምንሻልበትን (የተሻልንበትን) በዚያ ራሳችንን እንመለከታለን። እግዚአብሄር ግን የጠቅላላ እውቀት ሳይሆን የግል ጥያቄዎች ለእያንዳንዳችን አለው። አዎን እግዚአብሄር ዛሬም ጥያቄ አለው።
በተለይ የመንፈሳዊነት ጭምብል በበዛበት በአሁኑ ዘመን እግዚአብሄር ለእያንዳንዳችን ጥያቄ አለው። ከዚህ በታች ለሚቀጥሉት እግዚአብሄራዊ ለሆኑ ጥያቄዎች እውነተኛ የሆነ መልስ እንድንሰጥ በጌታ ፍቅር እጠይቃችኋለሁ። ማንም በማይሰማበት በግል ስፍራችን መልሱን ለጌታ እንመልስ፣ ከእርሱ ጋር እንስማማ፣ ጥያቄው ካልገባን ደግሞ ጌታ ሆይ አልገባኝም ብሎ በትህትና መጠየቅ ብልህነት ነው። ብልጣብልጥነት ለያዕቆብም አልበጀውም! እግዚአብሄር ዘልቆ ያያል፤ እግዚአብሄር አይታለልም፣ በፊታችን ላለው ረጅም ጉዞ አብሮ ለመጓዝ ለእግዚአብሄር ጥያቄዎች መልስ እንስጥ።
የእግዚአብሄር ጥያቄዎች
ወዴት ነህ? ዘፍ 3፥8-10
ይህ ጥያቄ እግዚአብሄር ካስቀመጠበት ስፍራ ለታጣው ለመጀመሪያው አዳም የቀረበ ጥያቄ ነበር። ይሁን እንጂ የዛሬይቱ ቤ/ክርስቲያንም ለዚህ ጥያቄ መልስ መስጠት ይገባታል!
- ዛሬም ይህ የወዴት ነህ ጥያቄ ለእያንዳንዳችን ነው። ዛሬ ራሳችንን ለቤ/ክርስቲያን፣ ለህብረት፣ ላለው ሲስተም ራሳችንን አስገኝተን ለእግዚአብሄር ግን ራሳችንን ሰውረን ይሆን? ለመደበቃችን ወይም እግዚአብሄር ባስቀመጠን ስፍራ ላለመገኘታችን እንደ ምክንያት አድርገን የምናቀርበው ነገር ይኖረን ይሆን? ግድ የለም ምክንያት ለአዳምም አልበጀውም፤ እዚህ ነኝ እንበለው።
አዳም ከስፍራው ለመልቀቁ ሚስቱን እንደምክንያት ቢያቀርብም ከመጠየቅ አልዳነም። ዛሬም ስፍራችንን ወይም እግዚአብሄር በወሰነልን ከፍታ ውስጥ ላለመገኘታችን ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩን ይችላሉ፣ እነዛ ሁሉ ከመጠየቅ አያድኑንም፤ ምክንያት ፈጣሪዎችም ይጠየቁበታል፤ ዛሬ ምክንያቶቻችንን ሁሉ አውልቀን እንጣል፣ አይኖቻችንን ከሰዎች ላይ አንስተን በእርሱ ላይ እናድርግ፤ ዛሬ በምን ውስጥ ነው ራሳችንን ሸሽገን ያለነው (ሰውረን ያለነው)? በአግልግሎት ውስጥ? ዛሬ ለዚህ እውነተኛ ጥያቄ እውነተኛ መልስ እንስጥ። በምንድነው ራሳችንን እያጽናናን ያለነው? ነገ በሚል? ነገ የኛ አይደለም ዛሬን እዚህ ነኝ እንበለው በተለያየ የሃጢዓት ልምምድ ውስጥ ያለን ነገሮችን ከመደጋገምና ምናለበት በሚል በድንዛዜ ውስጥ ያለን ዛሬ አድራሻችንን እንንገረው፤ ያለንበትን ስፍራ እንዳልወደድነው ፈቃዳችንን እንንገረው፤ ነጥቆ ሊያወጣን የታመነ ነው፥ እንውጣና አዲስ ኪዳን እናድርግ።
አዳም በቅጠል ራሱን ሸፍኖ ምክንያት እንደ ደረደረው ሁሉ ዛሬም እኛ በስራ፣ በኑሮ፣ በትምህርት፣ ራሳችንን ብንሸሽግም እግዚአብሄር ወዴት ነህ የሚለው የፈላጊነቱ ድምፅ እስካለንበት ይመጣል፤ ያኔ እዚህ ነኝ እንበለው ከእርሱም ጋር እንስማማ።
2. ለምን ፊትህ ጠቆረ? ዘፍ 4፥6-7
ይህ ጥያቄ ለአዳም ልጅ ለቃየል የቀረበ ጥያቄ ነው። በዘፍ 4 ላይ እንደምንመለከተው ሁለቱም ከአንድ አባት የተወለዱ ሲሆኑ ክፍሉ የሚያብራራልን ስለ አቤል መስዋዕት እንጂ ስለ ቃየል አይደለም። አቤል በኩሩንና ዋና የተባለውን ስጦታ ለእግዚአብሄር እንደሰጠ እናያለን። እግዚአብሄርም መስዋዕቱን ተመለከተ ወደ ቃየል መስዋዕት ግን አልተመለከተም። ከዚያ በኋላ የቃየል ፊት እንደጠቆረ መፅሀፍ ይነግረናል። ዛሬ ከአንድ አባት ተወልደን አንድ አይነት መስዋዕት እያቀረብን ከጎናችን ያለው ወንድም መስዋዕት የእግዚአብሄርን ትኩረት ይስብ ይሆን? ዋና ነገሩን በመዝራቱ በሰው ዘንድም በእግዚአብሄር ዘንድም ዋና በተባሉ ነገሮች ሲባረክ ስናይ ፊታችን ይጠቁር ይሆን? (ጠቁሮም ይሆን?) ወይስ በእግዚአብሄር ተናደን ይሆን? እኩል እያገለገልን፣ እኩል እየሮጥን፣ በሰውም በእግዚአብሄርም ፊት ሞገስ ሲያገኝ፣ የሚናገረው ሲሰማለት፣ ዝማሬውና ስብከቱ ሰው ሲባርክ፣ አቅዶ ሲሳካለት፣ እኔ ግን ለምን እያልን ተናደንና ተቆጥተን ይሆን? ፊታችን በሰዎች (በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ) ጠቁሮ ይሆን? ዛሬ ይህ ጥያቄ ለእኛም ነው። ለምን ፊትህ ጠቆረ? አንድ ምክር እንመካከር፥ ፀሎቱ ለምን እንደተሰማለት በሰውና በእግዚአብሄር ፊት ለምን ሞገስ እንደሆነለት፣ መስዋዕቱ ለምን በእግዚአብሄር ዘንድ መልካም መዓዛ እንደሆነለት ጠጋ ብለን ሚስጥሩን እንጠይቅና ከቀደሙት እንማር እንጂ ፊታችን አይጥቆር። ከኔ ይልቅ ወንድሜ ይሻላል እንበል እንጂ ወንድማችንን ለመግደል፣ በነገር ለመንደፍ፣ በሰው ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖረው የውሸት ድሪቶ አንደርትበት፤ እግዚአብሄርም እንዲል “መልካምን ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ሀጢዓት በደጅህ ታደባለች ፈቃዷም ወደ አንተ ነው አንተ ግን በእርሷ ንገስባት፤” ይህ ምክር ዛሬም ለእያንዳንዳችን ነው፤ በልባችን ውስጥ መልካምነት ሲጠፋ ለወንድሞቻችን ያለን አመለካከት ሲበላሽ ያኔ ሀጢዓት በደጅህ ነች ንገስባት የሚል ጥሪ ከእግዚአብሄር ዘንድ አለ፤ ይህ ለሆነብን እየሆነብንም ላለን ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም እንደዚህ ያሉ ነገሮች በልባችን ሲፈጠሩ ይህ መፅሀፍ ክፍል ትዝ ይበላችሁ። አሜን!
3. ወንድምህ ወዴት ነው?
አሁንም ለቃየል የቀረበ ጥያቄ ነው። ቃየል ወንድሙን ገድሎት ነበር፤ እግዚአብሄር የሰጠውን እድል ባለመጠቀሙ እግዚአብሄር በሁለተኛ ጥያቄ ወደ ቃየል መጣ፤ ወንድምህ ወዴት ነው በሚል ዛሬስ ወንድሞቻችን እህቶቻችን ወዴት ናቸው? እኛ በሰይፍ ላንገድላቸው እንችላለን፤ ዮሀንስ ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው ይላል፤ የጠላናቸው፣ ያማናቸው፣ ስማቸውን ያጠፋናቸው፣ ያደምንባቸው ካሉ፥ ዛሬም ይህ ጥያቄ ለእኛም ነው ከዚህ ነጻ ለሆንን ሰዎች እግዚአብሄርን አመሰግናለሁ፤ እንዲበዙልንም የዘወትር ፀሎቴ ነው፤ መልሳችን ላይ እንንጠንቀቅ! ውጤቱ ስለማያምር አሁንም ‘እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝ?’ አይሁን። አሁን ወደ ማስተዋላችን እንመለስና የቱጋ እንዳሉ እናስብ እንፈልጋቸውም። አዎ ዛሬ “እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝ፡“ ንሰሃ ገብተን ለሚቀጥለው እርምጃ እንዘጋጅ።
ይቀጥላል
ስንታየሁ መታፈሪያ