የጠፋብን ክብር
በዘመናችን ባለች ቤ/ክርስቲያን ውስጥ የእግዚአብሄር መገኘት ሳይኖር በሰዎች የተነደፉ ብልሀቶችና የአሰራር ስልቶች ድርጅታዊ መዋቅሮችና ስብሰባዎች ሞልተው ተትረፍርፈዋል። እንደውም በአሁኑ ሰዓት የእግዚአብሄር ቃል እንዲህና እንዲያ ስለሚል አሰራራችንን በዚህ መሰረት እናድርግ የሚለው አባባል እንደ አላዋቂነት እየተቆጠረና ከያዝነው የአሰራር ስልት ጋር አይሄድልንም እየተባለ ነው። ለእግዚአብሄር ቃል ቀላል ግምት በመስጠትና በእግዚአብሄር ቅዱስ ፍርሀት ውስጥ ባለመሆን ተገቢውን ዋጋ አለመስጠት ኦዛ ታቦቱን የተሸከሙትን በሬዎች ሲከተል እንደሆነበት መሆን ነው። ቤ/ክርስቲያን ለውጫዊው ታይታና ይህንንና ያንን ሰርተዋል የሚለውን ከሰዎች የሚሰጠውን ጥሩ አስተያየት ለማግኘት ከመቸውም የበለጠ ጥረት እየተደረገና እየተለፋ ያለበት ዘመን ላይ ደርሰናል።
እግዚአብሄር አምላካችን ግን ከመንፈሱ ያልሆነ ጥሩ አሰራሮችን ሁሉ አይደግፋቸውም። ይህ ማለት ግን እግዚአብሄር ጥሩ አሰራሮችን ይቃወማል ማለት አይደለም። ለሙሴ እንደተናገረው በዘፀዓት 25፥9 እኔ በማሳይህ እቅድ መሰረት ስሩት፤ እንዲሁም በዘካ 4፥6 በመንፈሴ እንጂ በሀይልና በብርታት አይደለም ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሄር። ጌታችን ኢየሱስ ሲናገር በዮሀንስ 5፥19 ላይ አብ ሲያደርግ ያየውን እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ አይችልም ይላል። ጌታችን ኢየሱስ እንኳ አባቱ ከሚያደርገውና ከሚያሳየው አሰራር ውጭ የራሱን ስልቶች ለመጠቀም አንድም ጊዜ አልሞከረም።
በዛሬው ፅሁፋችን ስለ እግዚአብሄር ታቦት መማረክ ስለሚያስተምረን 1ኛ ሳሙ 4፥3-22 ያለውን ክፍል አለፍ አለፍ እያልን እናየዋለን። ... ህዝቡም በመካከላችን እንዲሄድ ከጠላቶቻችንም እንዲያድነን የቃል ኪዳኑን ታቦት እናምጣ አሉ... ታቦቱም ከሁለቱ የኤሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሀስ ከሁለት ሀጢዓተኛ ልጆች ጋር በደረሰ ጊዜ እስራኤል ሁሉ ታላቅ እልልታ አደረጉ፤ ምድሪቱም አስተጋባች፤ ነገር ግን ያ ሁሉ ጩኽት አልረዳቸውም። እልም ያለና ግልፅ የሆነ ሀጢዓት ሲፈፀም ዝም ብለው ተቀብለው ነበር፤ ታቦቱ ያመጣላቸው ጥቅም አልነበረም፤ ምክንያቱም ክህነት ቆሟል፣ አገልጋዮች የእግዚአብሄርን አሰራርና መንገድ ትተዋል፤ ከዚህም የተነሳ እስራኤሎች ተሸነፉ፣ የእግዚአብሄር ታቦት ተማረከ። ኤሊም ስለ እግዚአብሄር ታቦት ልቡ ተናወጠ፤ ኤሊ ስለ ልጆቹ ሲሰማ ደህና ነበር፤ ስለ እግዚአብሄር ታቦት መማረክ በሰማ ጊዜ ከተቀመጠበት ወንበር ላይ ወድቆ አንገቱ ተሰብሮ ሞተ። የፊንሀስም ሚስት ምጥ ይዟት ለመውለድ ሀይል ቢኖራትም፣ የእግዚአብሄር ታቦት ስለተማረከ ክብር ከእስራኤል ለቀቀ ስትል የህፃኑን ስም ኢካቦድ ብላ ጠራችው።
ዛሬ ጠላት አሳውሮናል የታቦቱ በመካከላችን መኖር ትልቁ ሚስጢር ምንድን ነው? መፈራቱ ነው፣ መከበሩ ነው፤ ዛሬ መፍራታችን ወዴት አለ? ማክበራችንስ የታለ? ጠላት ስቆብናል፤ ፍቅራችንን ወስዶ በምትኩ ወንድሞቻችንን እንድንጠላ ሰላም አትበሏቸው፣ ወደ እነርሱም ጉባኤ አትሂዱ እየተባለ ነው። አሕዛብ በፍቅራችሁ ያውቋችኋል የተባለልን ነበርን፤ ዛሬ ግን በተቃራኒ መንገድ እያወቁን ነwe ዮሐ 13፥35:: በዚህ ንስሀ ስንገባ የአምላካችን አሰራሩንና መንገዱን ችላ በማለት የመልሶ ማቋቋም ኮንፍራንሶችን እናደርጋለን። ነገር ግን በኤካቦድ የሚደረጉ ኮንፍራንሶች የመፅናናት ልጆችን አይወልዱም፤ እልልታና ጩኽት ሊኖር ይችላል፣ መገለጥ የሚመስሉ ነገሮች ሊነገሩ ይችላል፤ ሆኖም ግን ድል የለም፤ ምክንያቱም ፍቅር የለም፣ ይቅርታ የለም፣ በወንድማማች መካከል ፀብ ይዘራል፣ ይህ ደግሞ እግዚአብሄር ነፍሴ አጥብቃ ትፀየፈዋለች ይላል። (ምሳ 5፥19)
ዛሬ እንደሸመገለው ኤሊ አይኖቻችን ፈዘዋል፣ በሸመገሉና ዕድሜአቸው 98 ዓመት በሆነ ስርዓቶችና መንፈሳዊ ልምምዶች ተይዘናል፣ ስንቶች መንፈሳዊ ስራ ከብዷቸው በሽታ ሆኖባቸዋል። በተቀደሰ የእግዚአብሄር ቃል አሰራር ውስጥ ስለሌሉ መንፈሳዊ አገልግሎት ከጌታ ፀጋ የተነሳ ሊቀላቸው ሲገባ ሸክም ሆኖባቸዋል። ልንመለስና የአምላችንን ቃል ልንመረምር ይገባናል፣ እርሱ በዚህ መንገድ እንድንሄድ አልተናገረንም፤ መንገዳችንን እንመርምርና እንፈትን። ወደ እግዚአብሄርም እንመለስ ልባችንን ከእጃችን ጋር በሰማይ ወዳለው ወደ እግዚአብሄር እናንሳ:: (ሰቆ ኤር 3፥40-46) ይህ ያዋጣናል፤ የእግዚአብሄርንም ጉብኝት ያመጣልናል፤ የጠፋው ነገራችን ሁሉ ይመለሳል። ታቦቱን ለመመልከት በኢያሱ መፅሀፍ ላይ መመልከት ይቻላል። ኢያሱ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብሎ ነገራቸው፣ የእግዚአብሄር ባሪያ ሙሴ እንዲህ ብሎ ያዘዛችሁን ቃል አስቡ፤ አምላካችሁ እግዚአብሄር ያሳርፋችኋል፤ ይህችንም ምድር ይሰጣችኋል። (ኢያ 1፥13)
እግዚአብሄር ቀይ ባህርን እንዴት እንደከፈለ ከዚህ በፊት ሰምተዋል። በእግዚአብሄር ባሪያ በሙሴ የተከናወኑትን ተዓምራት ሁሉ ሰምተዋል። ነገር ግን ሙሴ ሞቷል፤ የዘላለም አምላክ ግን በዙፋኑ ላይ ነበር። ሕዝቡን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊመራ ዝግጁ ነበር፤ ተስፋ የተገባላቸው ሁሉ እንዲወርሱ፤ ዮርዳኖስን ሊያሻግራቸው ነው። ዮርዳኖስን ለመሻገር ወደፊት በተንቀሳቀሱ ቁጥር የቃል ኪዳኑ ታቦት ታላቅ ነገር ይሰራ ነበር። የአምላካችሁን የእግዚአብሄርን የቃል ኪዳን ታቦት ሌዋውያንና ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ ከሰፈራችሁ ተነስታችሁ ተከተሉት። (ኢያ 3፥3-8)ኢያሱ ካዘዘው ትዕዛዝ ውስጥ በጣም ልብ የሚነካው አይናችሁን በታቦቱ ላይ አድርጉ የሚለው ነው። አይናቸውን በታቦቱ ላይ በማድረጋቸው ዮርዳኖስ ተከፍሎ በደረቅ ምድር ተሻገሩ፤ ታቦቱን እስከ ተከተሉበት ጊዜ ድረስ አሸናፊዎች ነበሩ፤ የቃል ኪዳኑን ታቦት እየተከተሉ የኢያሪኮን ከተማ በመዞር ጩኽትና እምቢልታን በማሰማት የኢያሪኮ ግንብ ሲፈርስ በአይናቸው አዩ። ኢያ 6፥1-16 አምላካችንን በመስማትና በመታዘዝ ስንሄድ በሕይወት ጉዟችን ላይ የቆሙ ተራሮች ደልዳላ ሜዳ ይሆናሉ።ዘካ 4፥7
የቃል ኪዳኑ ታቦት ለእኛ ኢየሱስ ነው። እግዚአብሄር አምላካችን ስለ ልጁ ሲመሰክር እንዲህ ብሏል፥ የምወደው ልጄ እርሱ ነው እርሱን ስሙት። (ማቴ 17፥5) እንድንሰማው፣ እንድንከተለውና አሰራሮቹን እውን እንድናደርግ የተሰጠን ታቦታችን ኢየሱስ ይህ ነው።
ኢዮብ ከእግዚአብሄር ሀሳብ ጋር እንድንስማማ እንዲህ ይለናል፤ አሁንም ከእርሱ ጋር ተስማማ ሰላምም ይኑርህ። (ኢዮ 22፥21-25)
ዛሬ የምንከተለው ኢየሱስ የፍቅር አምላክ ነው፣ የእውነትና የሰላም አለቃ ነው፣ ራሱን አሳልፎ የሰጠን ስለ ፍቅር ነው። በዚህ ውስጥ የእኛ የሕይወት ምልልስ እንዴት ነው?
የእግዚአብሄር ፀጋ ያግዘን
ኤልያስ
ከሳክራሜንቶ