እቀብተ-እምነት (Apologetics)
“ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።” 1ኛ ጴጥ. 3፡15
መቼም የክርስትናችን እውነተኛነትና ህያውነት ከተለያየ አቅጣጫ እየተበጠረ (scrutinize እየተደረገ) መሆኑን በየለት ተለት ህይወታችን የምናስተውለው ጉዳይ ነው። እንደውም አሁን ባለንበት ዘመን በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የክርስትና መሰረታዊ እውነቶች ላይ መዘባበትና ማላገጥ (mockery) እንደ ጤነኛ እና ዘናጭ (cool) ነገር መታየት ጀምሯል። ብዙዎች በክርስትና ላይ እያላገጡ ተናግረው ታዋቂ ሆነዋል፤ እያሾፉ ጽፈው መጽሃፍቶቻቸው በኒው ዮርክ ታይምስ የመጽሃፍት ሽያጭ ሰንጠረዥ አናት ላይ ለረጅም ጊዜ ተቀምጠዋል፤ እየተዘባበቱ ፊልም ሰርተው ፊልሞቻቸው የቲያትር ቤቶችን አዳራሾች አጨናንቀዋል። አያሌ የፍልስፍና (የፍል-ስንፍና) አዋቂዎችና በምድር ዙሪያ ያሉ ሃሳባውያን የመጽሃፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በመሰነጣጠቅና አንዱን ከአንዱ ጋር በማምታታት ላይ ናቸው- እርስ በእርሳቸው የሚቃረኑ (contradictory) ሃሳቦችን ለማግኘት በከፍተኛ ሩጫ ላይ ናቸው። አርኪዮሎጂስቶች በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ የሚገኙ ጥንታዊ ከተሞችን ከላይ እስከታች እየበረበሩ ናቸው- የኢየሱስን ህያውነት የሚፃረሩ ግኝቶችን አግኝተው የክርስትያኖችን ወሽመጥ ሊበጥሱ አሰሳቸውን ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ገፍተውበታል! ሳይንቲስቶች በቤተ-ሙከራዎቻቸው የሚያሳልፏቸውን ቀናትና ሰዓታት ጨምረዋል- የተፈጠራችሁት በእግዚአብሄር መለኰታዊ ትዕዛዝ ሳይሆን በblue green algae (አማርኛውን እናንተው ፈልጉለት) አዝጋሚ የዕድገት ሂደት ነው ብለው ሊያረዱን ቛምጠዋል። ወገኖቼ፡ ወደድንም ጠላንም፣ አወቅነውም አላወቅነውም፣ ነቃንም ተኛንም ክርስትናችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተጠቃ ያለበት ዘመን ነው።
ታዲያ እነዚህ ሁሉ “የሚንበለበሉ ፍላጻዎች” ባሉበት በዚህ ዘመን አቃቤ እምነት (apologetic) መሆን ይቻላል? “የዚህ ዓለም ልጆች በአባታቸው በዲያቢሎስ ስፖንሰር አድራጊነትና በስጋቸው አቅራቢነት የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ሁሉ ለመመለስ እንችላለን? እንደ ክርስትያንስ እንዴት ነው እምነታችንን መከላከል የምንችለው? ነውስ እጆቻችንን አጣጥፈን፣ የአይኖቻችንን ቆቦች እንዳላየ ከድነንና ጆሮ ዳባ ልበስ ብለን እንቀመጥ? ወይስ እለት ተለት የእምነት አቃቢያን ለመሆን እራሳችንን እናሰልጥን?
የዚህች አጭር ጽሁፍ አላማ ሁሉንም ጥያቄዎች አብራርቶ ለመመለስ አይደለም። በአጭሩ ግን፦ አዎን፤ በዚህ ዘመንም አቃቤ- እምነት (የእምነት ጠበቃ) መሆን ይቻላል። በፍጹም፤ እጆቻችንን አጣጥፈን፣ አይኖቻችንን እንዳላየ- ጆሮዎቻችንን እንዳልሰማ ዘግተን መቀመጥ የለብንም። እምነታችንን ዛሬም አባቶች እንዳተከላከሉት መከላከን እንችላለን፤ ስለ ተሰጠን የተስፋ ቃልም የሚነሱብንን ጥያቄዎች ለመመለስ ይቻላል!
ምነው ወንድም ግዮን “ፉከራ” አስመሰልከው እኰ- የሚቻል ከሆነ እንዴት እንደሚቻል ለምን አትናገርም? እንዳምትሉኝ እርግጠኛ ነኝ። ወይም ደግሞ “አ..ዬ አሁን እኰ ‘እንዴት’ ብንለው ያቺን የፈረደባትን ‘ሃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ’ የምትለዋን ጥቅስ ሊጠቅስ ነው።” እያላችሁ የምትታዘቡኝ አንባቢያን እንደምትኖሩ አልጠራጠርም።
እንዴት ማለት ጥሩ! መቼም እንደ ሙስሊሞች እምነታችንን የሚዳፈሩትን እያሳደድን እንግደል እንደማልል ሳትገምቱ አትቀሩም። የፊርማ ማሰባሰቢያ ቅጽ አዘጋጅተን እናዙር እና ተቃውሞአችንን እናሳውቅ ለማለትም አይደለም። ይልቁን እራሳችንን የእምነት አቃቢያን ለማድረግ ስናሰለጥን ማድረግ ካሉብን በርካታ ነገሮች ሁለቱን በአጭሩ ለማተት ነው።
ስለ መጽሃፍ ቅዱስ ያለውን ብዥታ ማጥራት
በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ። (2ኛ ጴጥ 2፡16)
ብዙ ሃሳባውያንና የፍልስፍና ጠበብት የእግዚአብሄርን ቃል እየሰነጣጠቁ በቁንጽል (ውሱን) እውቀትና መረጃ ክርስትናን ለማጥቃት ከመነሳታቸው ጀርባ ያለው ምስጢር አንድና አንድ ነው- ስለ መጽሃፍ ቅዱስ ምንነት፣ ተልዕኰና ይዘት ያላቸው አመለካከት የተዛባ/የተጣመመ መሆኑ። እንደ ክርስትያን መጀመሪያ ማድረግ ያለብንም ይሄንን ብዥታ ማጥራት ነው። ይሄንን ለማድረግ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል ጠንቅቀን ማወቅ አለብን! መጽሃፍ ቅዱሳችንን ጊዜ እየሰጡ በማጥናት ጠንቅቀን ማወቅ ለክርስትያኖች አማራጭ የሌለው ነገር ነው። ስለ እያንዳንዱ ክፍል ተልዕኰ፣ ይዘትና የተጻፈበትን ታሪካዊ ዳራ በጥንቃቄ ማወቅ የሚነሱትን ጥያቄዎች ለመመለስ ብቻ ሳይሆን መስመር የሳቱና የማይሄዱ ጥያቄዎችንም ለመለየት ይረዳናል። በመቀጠልም ስለ መጽሐፍ ቅዱሳችን የሚከተሉትን መሠረታዊ ጭብጦች ማሳወቅ ይጠበቅብናል፦
ሀ. መጽሐፍ ቅዱስ “የመዳን መጽሐፍ” (Book of Salvation) ብቻ መሆኑን እያስረገጡ መናገር። መጽሐፍ ቅዱስ የነሱን የመፈላሰፍ ጥማት ለማርካትና በዓለም ላይ ላሉ ሃሳባዊ አምባጓሮዎች ሁሉ መልስ ለመስጠት ታስቦ የተጻፈ መጽሐፍ እንዳልሆነ ማስረዳት (2ኛ ጢሞ. 3፡15) ፤
ለ. በጥቃቅን ጥቅሶችና ታሪኮች ላይ ከማተኰች ይልቅ ጠለቅ ያለ መረዳትን በሚሰጡ ሙሉ ሃሳቦችና አገባቦች (context) ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ መምከር፤
ሐ. የመጽሐፍ ቅዱስ መካከለኛ ፀሃፊዎቹ፣ የተፃፈላቸው ሰዎችና ማህበረሰቦች፣ ወይም ደግሞ አንባቢዎቹ ሳይሆኑ ክርስቶስ እንደሆነ ደግሞ ደጋግሞ ማስረዳት (ዮሐ. 5፡39) ፤
መ. ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስን የፃፉት ሰዎች ቢሆኑም የጻፉት በመንፈስ ተመርተው ስለሆነ በእያንዳንዱ ጽሑፍ ውስጥ የሚንፀባረቀው የእግዚአብሄር ሃሳብ እንደሆነ ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ሌሎች የስነ-ጽሑፍ ስራዎች (literatures) በምድራዊ የሰዋሰው (grammar) ህግጋትና የመመዘኛ መስፈርቶች ለመገምገም መሞከር መለኰታዊ የሆነውን ሃሳብ እንደሚያስት አበክሮ መናገር ያስፈልጋል። አንድ ሰው መጽሃፍ ቅዱስን ከማንበቡ በፊት ይሄንን ሰዋዊ መነጽር አውልቆ በዉስጡ ያሉትን መጽሓፍት እንደ “የህይወት ቃል” ለማንበብ መዘጋጀት አለበት። ይሄን ካላደረገና የሼክስፒርን ስራዎች በሚያነብበት መነጽር መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ቢጀምር- የዳዊትን የቅኔ ችሎታ፣ የሙሴን የህግ አረቃቀቅ ክህሎት፣ የሳሙኤልንና የሉቃስን የታሪክ ዕውቀትና የማስታወስ ብቃት፣ የማርቆስን አዝናኝ የአፃፃፍ ስልት፣ እና የዮሐንስን ፍልስፍናዊ የአፃፃፍ ዘይቤ አድንቆ ወይም ነቅፎ ብቻ ይጨርሳል እንጂ አንድም ለህይወቱ የሚቀርለት ነገር አይኖርም።
ሠ. ከላይ እንደተባለው ጸሃፊዎቹ በመንፈስ እየተመሩ ስለፃፉት መጽሐፍ ቅዱስ መለኰታዊ ዶሴ (divine document) ነው። አንድ ሰው አንብቦት ሊረዳውና ሊያምነው ብሎም ሊተገብረው የሚችለው ጽሑፉ ከተፃፈበት መንፈሳዊ መንግስት ጋር ጤነኛ የሆነ ግንኙነት ሲኖረውና መንፈስ ቅዱስም ሲረዳው ነው። አለበለዚያ ሁሉም ነገር ቀልድ ቢመስለው፣ ቢወሳሰብበትና ባይገባው አይገርምም። ለዚህ ነው፡ እነሱ አንብበው በሽሙጥ ከንፈራቸውን የሚያጣምሙበትን መጽሐፍ እኛ አንብበነው በመደነቅ እጃችንን አፋችን ላይ የምናደርገው። ለዚህ ነው፤ እነሱ አንብበው በምጸት የሚስቁበትን መጽሐፍ እኛ አንብበነው በተመስጦ የምናለቅሰው። ለዚህ ነው፤ እነሱ ሲያነቡት በንቀት ሞልቶ “እንዲህ አይነት አምላክ የለም” የሚያስብላቸውን መጽሐፍ እኛ አንብበን በፍርሃት እና በመንቀጥቀጥ የአምላካችንን ህያውነት የምናምነው።
እነዚህን 5 መሠረታዊ እውነቶች ማስጨበጥ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያሉ ብዥታዎችን ለማስወገድ እጅጉን ይረዳል።
የሚያዋጣው መከላከያ፡ ውይይቱን፣ ጥያቄዎቹንና አጀንዳዎቹን ከሃሳባዊነት ላይ ነቅሎ ወደ ተጨባጭ የህይወት ፍሬ እና እንቅስቃሴ ማሳደግ
መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። (ማቴ. 5፡16)
ሃሳቦችን ሁሉ ተነጋግሮ መቋጨት አይቻልም። የሰው ልጅ ሃሳብ ተሰፍሮ፣ ተቆጥሮና ተተንትኖ አያልቅም። ስለዚህ የሚነሱ ሃሳቦችን ሁሉ ለመመለስ መሞከር እጅግ የዋህነት ብቻ ሳይሆን የማያዋጣ አካሄድም ጭምር ነው። ስለዚህ እንደ ክርስትያን በህይወታችን ጥራት እምነታችንን መከላከል ይጠበቅብናል። ይሄን የምናደርገው ደግሞ ምን ያህል የክርስትና እውነቶች በህይወታችን ፍሬያማ እንደሆኑ በማሳየት ነው። በክርስትና ውስጥ የተካተቱት እውነቶችን እውነተኛነት ለሌሎች ለማሳየት የመጀመሪያው እርምጃ እውነቶቹ ለኛ ምን ያህል እንደሰሩልን ለዓለም ማሳየት መሆን አለበት (pragmatic truth ይሉታል ፈላስፎቹ)። እግዚአብሔር ደግሞ ይረዳናል!!
ጌታ ቢፈቅድና ብንኖር በሌላ ጊዜ ሌሎች የመከላከያ መንገዶችን ለመዳሰስ እሞክራለሁ። ለዛሬው ግን ሁላችንም መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና ያሉትን የተዛቡ አመለካከቶች በማጥራት እንዳዚሁም ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ቃል በሆነ የብርሃን ህይወት የእምነት አቃቢያን (ጠበቆች) ለመሆን እራሳችንን እናሰልጥን እያልኩ እሰናበታችኋለሁ!!
ተባርካችሁ ቅሩ!
ግዮን