ሰውና እንስሳት
በራሱ ምሳሌ እግዚአብሔር ሲፈጥረን፣
ከምድር አፈር ጭቃ ያኔ ሲያበጃጀን፣
በምድር በሰማይ ያሉትን ፍጥረታት፣
ወፎችን አሦችን ሌሎችም እንስሳት፣
እንድንገዛ ብሎ እንድናስተዳድር፣
እንደራሴ እንድንሆን ለሰማይ በምድር፣
ነበረ ሃሳቡ እሱ እኛን ሲፈጥር።
ያን ጊዜ ዛዲያ እኛና እግዚአብሔር፣
ግንኙነታችን ፍጹም መልካም ነበር።
አቤት ስንፈራው እሱም ሲያስብልን፣
በግብርም በመልክም ነበር አባታችን፣
ፍጹም ሰማያዊ ነበር እይታችን።
ታዲያ ይህን መሳይ ፍጹም ግንኙነት፣
በክፉ ምኞት ጦስ ነፋስ ነፈሰበት።
በመጠራጠሯ እናታችን ሄዋን፣
ባለመታዘዙ አዳም አባታችን፣
ያ ፍጹሙ ህብረት ከቶ ተበላሸ፣
መንፈሳዊው ነገር ከኛ ጥሎ ሸሸ።
እይታችን ሁሉ
ህብረታችን ሁሉ
ሆኖ ብቻ ቀረ ከስጋ ለስጋ፣
ከቶውን አልቻለም ፍጥረት ሊረጋጋ።
ያን ጊዜ ታዲያ ያለም ፍጥረታቱ፣
ጅብ አንበሳ ነብር ሞላው አራዊቱ፣
አለመታዘዝን ከገዢያቸው ወርሰው፣
መጠራጠርንም እንደ ሸማ ለብሰው፣
ጥርሳቸውንና ጥፍራቸውን ስለው፣
ሊያጠፉን ተነሱ ፊታቸውን ዞረው፣
የዘሩትን ማጨድ ቢሉ እንግዲህ ይህ ነው።