ወንጌል ዋጋ ያስከፍላል 2
ካለፈው የቀጠለ
ባለፈው እትም ላይ ወንጌል ዋጋ ያስከፍላል በሚል ርዕስ ተከታታይነት ያለው ፅሁፍ ይዤላችሁ ቀርቤ ነበር። ፅሁፉም በ15ኛው ክፍለ ዘመን ቤ/ክርስቲያን በተለይ በጆን ኸስ ሕይወት፣ አገልግሎትና የመስዋዕትነት ኑሮ ላይ ያተኮረ ነበር። በዚህ ፅሁፌ ይዤላችሁ የቀረብኩት በመጀመሪያ ክፍለ ዘመን በነበሩ በወንጌል አርበኞች የሰማዕትነት ሕይወት ዙሪያ ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ ለጴጥሮስ በዚች ዓለት ላይ ቤ/ክርስቲያኔን እመሰርታለሁ፤ የገሀነም ደጆችም አይቋቋሟትም አለው። ቤ/ክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስ አካልና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ ሙላቱ ናት። የእግዚአብሄርን ፈቃድ፣ ሃሳብ፣ ክብርና ኅይል መገለጫና ሰማይን በምድር ላይ ወክላ የምትንቀሳቀስ ናት። ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ እሳትን ልጥል መጣሁ ከነደደ ምን እፈልጋለሁ አለ። ኢየሱስ የወንጌልን እሳት ጣለ፤ በደሙም አንቦገቦገው። ለአካሉም ማለትም ለቤ/ክርስቲያን የወንጌሉን ችቦ አስረክቦ የመንፈስ ቅዱስንም ሀይል አስታጥቆ በአባቱ ዘንድ በላይ በሰማይ አለ። ይህን የተረዱት ሐዋሪያት ኑሮአቸውን፣ ስራቸውን፣ ጊዜአቸውን፣ ምቾቶቻቸውን ሰውተው እስከመጨረሻው የወንጌልን ችቦ ይዘው ሮጡ። እነርሱም እንደጌታቸው በደማቸው አንቦግቡገው ለተተኪው ትውልድ አስረክበው አለፉ። የገሃነም ደጆች ማለትም ሰይጣን በተለያየ ዘመን መንግስታትን፣ የአገር ገዢዎችን፣ መሳፍንትን፣ መኳንንትና የሃይማኖት መሪዎችን በማስነሳት የወንጌሉ ችቦ እንዳይነድ ለማጥፋት ሞክሮ ነበር። ዛሬም ደግሞ ከመሞከር ወደ ኋላ አላለም፤ ነገር ግን “የገሀነም ደጆች አይቋቋሟትም” ከሚለው ከቃሉ እውነተኛነት፣ ከእግዚአብሄር ታማኝነት፣ ከመንፈስ ቅዱስ እርዳታና በነፍሳቸው ተወራርደው በዘመናት መካከል የወንጌሉን ችቦ ከትውልድ ወደ ትውልድ እያስተላለፉ ካሉ ቅዱሳን የተነሳ ሊጠፋ ጭል ጭል ያለበት ዘመን ቢኖርም እንኳ እግዚአብሄር ይመስገን እስከዛሬም እየነደደ አለ።
በመጀመሪያ ክፍለ ዘመን የወንጌሉን ችቦ በደማቸው አቀጣጥለው ካለፉት የእምነት አርበኞች ጥቂቶቹን እናያለን።
እስጢፋኖስ - በመጀመሪያው ቤ/ክርስቲያን በዲቁና ያገለገለ መንፈስ ቅዱስና እምነት የሞላበት ሰው ነበር። ይህ ሰው በኢየሩሳሌም ከተማ በከሀዲዎች፣ በተጠራጣሪዎች፣ በሃይማኖተኞችና የሀይማኖት መሪዎች ነን ባዮች ፊት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንስኤ በግልጥ ሲናገር በድንጋይ ተወግሮ አለፈ። ሐዋ 7
ያዕቆብ - የዘብዴዎስ ልጅ የዮሐንስ ታላቅ ወንድም የማሪያም (የኢየሱስ እናት) ዘመድ የሆነችው የሰሎሜ ልጅ የሆነው ስለወንጌል በሄሮድስ እጅ አንገቱ ተቆርጦ አለፈ። ሐዋ 12
ፊሊጶስ - የገሊላ ቤተሳይዳ ተወላጅ የሆነውና በመጀመሪያ ደቀመዝሙር ተብሎ የተጠራው በላይኛው እስያ የወንጌልን ስራ በትጋት ሰርቶ በፍርግያ ብዙ መከራ ተቀብሎ ታስሮ በ54 ዓ.ም. ተሰቅሎ ሞተ።
ማቴዎስ - የናዝሬት ተወላጅ የሆነው ቀረጥ ሰብሳቢው የማቴዎስ ወንጌልን ፃፈ። በተጨማሪም በግብፅና በኢትዮጵያ ወንጌልን ሰብኮ በኢትዮጵያ በጦር ተወግቶ አለፈ።
ያዕቆብ (የኢየሱስ ወንድም) - የመጀመሪያው የእየሩሳሌም ቤ/ክርስቲያን መሪ (ጳጳስ) ሆኖ አገለገለ፣ የያዕቆብንም መልዕክት ፃፈ። መላው ዘመኑን ወንጌልን ሲሰብክና ሲያስተምር ኖሮ የ98 ዓመት ሽማግሌ ሆኖ ሳለ ወንጌልን በአደባባይ በግልፅ ሲሰብክ የተበሳጩ አይሁዶች በድንጋይ ወግረው ጭንቅላቱን በመጥረቢያ ለሁለት ተርትረውት ህይወቱ አለፈ።
ማቲያስ - ሐዋሪያት ዕጣ ተጣጥለው በአስቆርቱ ይሁዳ ምትክ የተተካው ወንጌልን ሲሰብክ በእየሩሳሌም ከተማ በድንጋይ ተወግሮ አንገቱን በሰይፍ ተቆርጦ አለፈ።
እንድሪያስ - የጴጥሮስ ወንድም ወንጌልን በእስያ አገሮች ሁሉ ሰብኮ ወደ ግሪክ መጥቶ እዚያ ወንጌልን ሲሰብክ ይዘው ሰቀሉት።
ማርቆስ - የማርቆስ ወንጌልን ፃፈ። በግብፅ ጣዖትን ለማምለክ ተሰብስበው ለነበሩ ወንጌልን ሲሰብክ ለአምላካቸው ቀንተው ቁጣቸው በእርሱ ላይ ነድዶ ወደ መሀል አስገብተው ከዚህና ከዚያ ሲጎትቱና ሲያንገላቱት ህይወቱ አለፈ።
ጴጥሮስ - ይህ አንጋፋ ሐዋሪያ ወንጌልን በድፍረትና በኅይል ሰበከ። ቤ/ክርስቲያንን በተለያየ ቦታ አደራጀ። በሮም ከተማ ሳለ ቄሳር ሊገድለው ነገር እየፈለገበት እንዳለ ቅዱሳን ሰምተው ሮምን ለቅቆ እንዲወጣ ወተወቱት። ጴጥሮስም ከሮም ሲወጣ በከተማይቱ በር ላይ ከኢየሱስ ጋር ተገናኙ። ጴጥሮስም ሰገደና ጌታ ሆይ ወዴት ትሄዳለህ ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም እንደገና እሰቀል ዘንድ ወደ ሮም እየሄድኩ ነው ሲለው ጴጥሮስም ተፀፅቶ ወዲያውኑ ወደ ሮም ተመለሰ። እርሱም ሮም እንደደረሰ ያዙትና የስቅላትም ሞት ተፈረደበት። እነርሱም ሊሰቅሉት ሲሉ እንደጌታዪ እሰቀል ዘንድ አይገባኝም፣ እባካችሁ ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ ብሎአቸው ተዘቅዝቆ ተስቅሎ ህይወቱ አለፈ።
ጳውሎስ - ስለወንጌል ተገረፈ፣ ታሰረ፣ በድንጋይ ተወገረ፣ ሞቷል ተብሎ ከከተማ ውጪ ተጥሎ እግዚአብሄር በእርሱ የጀመረው ስራ ስላልተፈፀመ ደህና ሆኖ በሕይወት ወደ ከተማ ገባ። ይህ የወንጌል አርበኛ የእምነት ጀግና የወንጌሉን ችቦ በዘመኑ ቦግ አድርጎ አቀጣጠለ። እስራት፣ ራብ፣ ግርፋት፣ ስደት አልበገረውም። በስብከቱ፣ በትምህርቱ፣ በፅሁፎቹም የመጓጓዣና የመገናኛ ብዙሃን ስልጣኔ ባልነበረበት በዚያ ዘመን ይታወቅ የነበረውን ዓለም ደረሰ። የሃይማኖት መሪዎች፣ ፈላስፎች፣ የሕዝብ መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ነገስታትን ጭምር በትምህርቱ መሠረታቸውን አናጋ አናወጠ። አብዛኛውን የአዲስ ኪዳን መፅሐፍትን ፃፈ። ፅሑፎቹም ካላቸው ጥልቅ የመለኮታዊ ምስጢር ገላጭነት ይዘት የተነሳ እስከዛሬ በዓለም ዙሪያ ሁሉ ይነበባል፥ ይጠናል። ለብዙዎችም ሕይወት መለወጥና ማደግ ምክንያት ሆኗል። እንግዲህ ይህ ሰው ወንጌልን ሲሰብክ ስለወንጌል አንገቱ በሰይፍ ተቆርጦ አለፈ።
ይሁዳ-ታዴዎስ - በመባል የሚታወቀው የያዕቆብ ወንድም በግሪክ ከተማ ወንጌልን ሲሰበክ ተሰቅሎ አለፈ።
በርተሎሜዎስ - በብዙ አገሮች ወንጌልን ሰበከ፣ ወደ ሕንድም ሄዶ ወንጌልን ሰበከ፣ ያመኑትንም አፀና፣ የማቴዎስ ወንጌልንም ወደ ሕንድ ቋንቋ ተረጎመ። ድርጊቱ ያበሳጫቸው ጣዖት አምላኪዎች መሃል አስገብተው ደብድበው ሰቀሉት።
ቶማስ (ዲዲሞስ) - ተጠራጣሪ በመባል የሚታወቀው በሞቱ ጌታውን አከበረ። በሕንድ ከተማ በከሃዲዎችና ጣዖትን አምላኪዎች ፊት የኢየሱስን ሞትና ትንሳኤ በግልፅ ሲያውጅ በጦር ተወግቶ አለፈ።
ሉቃስ - የሉቃስን ወንጌልና የሐዋሪያት ስራን ፃፈ። ከጳውሎስ ጋር በተለያዩ አገሮች ወንጌልን ሰበከ፤ በግሪክ አገር ወንጌልን ሲሰብክ የጣዖት አምልኮ ካህናት በወይራ ዛፍ ላይ ሰቀሉት።
ስምዖን (ቀናተኛው) - ወንጌልን በአፍሪካና በእንግሊዝ ሰብኮ በእንግሊዝ አገር ወንጌልን ሰለሰበከ ሰቀሉት።
ዮሐንስ (የዘብዴዎስ ልጅ) - የሰምርኔስ፣ የጴርጋሞን፣ የሰርዴስ፣ የፊላደልፊያ፣ የሎዶቂያና የትያጥሮንን አብያት ክርስቲያናትን እንደመሰረተ ይታመናል። ከኤፌሶን ወደ ሮም ሲጓዝ ተቃዋሚዎች ይዘው በፈላ ዘይት ውስጥ ጣሉት፤ ነገር ግን ምንም ሳይሆን በተዓምር ከዚያ አመለጠ። ቀሪው ዘመኑንም በፍጥሞስ ደሴት በስደት ኖረ። እዚያም ሳለ የዮሐንስ ራዕይን ፃፈ። ከሐዋሪያት መካከል ይህ ሰው ብቻ ሸምግሎ ወደጌታ ተሰበሰበ።
የእግዚአብሄር ቃል በራዕይ 14፥13 “ከሰማይም፥ ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ብፁዓን ናቸው። መንፈስ - አዎን ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ ስራቸው ይከተላቸው ብለህ ፃፍ የሚል ድምፅ ሰማሁ።” ይህ አባባል ሞት የማይቀር እንደሆነና ሁለት ዓይነት ሞት እንዳለ፥ አንደኛ በጌታ ሆኖ ሌላኛው ከጌታ ውጭ ነው። በጌታ ሆኖ መሞት መታደል (ብፅዕና) ነው።
በተጨማሪም ከድካሙ የሚያርፍ የሚሰራ ሰው ነው፥ ስራቸው ደግሞ ከመቃብር በታች የሚቀር ሳይሆን ከሞት ባሻገር እንደሚከተላቸው ይህ የመፅሀፍ ቅዱስ ክፍል ያሳየናል። አብዛኞቻችን በዚህ ዓለም የምንደክምባቸው ስራዎች ከመቃብር በታች ይቀራሉ፤ ነገር ግን ከላይ ያየናቸው የእምነት ጀግኖች ድካማቸው በምድር ላይ ለራሳቸው መልካም ስምን ለማኖር ሳይሆን የእግዚአብሔርን መንግስት ለማስፋት ወደ ሞት የሚነዱትን ለመታደግ ሊታረዱ የተወሰኑትን ለማዳን በጌታ ቀን የሚመኩበትን አክሊል ለማፍራት ነበር።
ለመሆኑ ዛሬ እኛ ድካማችን ምን ላይ ነው? ዛሬስ ወንድሜ እህቴ ለመሆኑ በጌታ ነህ/ነሽ? ደግሞ ድካማችን ምን ላይ ነው? ትኩረታችንን እናስተካክል፣ ከጊዜው ወደዘላለማዊ፣ በዚህ በሚያልፈው ዘመናችን የማያልፈውን ስራ ሰርተን ከላይ እንዳየናቸው አንደአባቶቻችን ለማለፍ እንወስን። አባቶቻችን ምርጫ ነበራቸው፣ ምርጫቸው ግን ያን መንገድና ሕይወት ሆነ። ዛሬም እኛም ምርጫችን ጌታንና ስራውን ይሁንልን።