ወንጌል ዋጋ ያስከፍላል 1
ሮም የጳጳሱ መናገሻ የነበረበትና ጊዜውም 15ኛው ክፍለ ዘመን ነበር ። በመላው አውሮፓ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የሚተዳደሩት በእርሱና እርሱ በሚወክላቸው ካርዲናል (Cardinal) አርክቢሾፕ (Archbishop) ቢሾፕና (Bishop) ካህናት ናቸው። መንፈሳዊ አገልግሎቶች ይሰጥ የነበረው በላቲን ቋንቋ ሲሆን ቅዱስ ቁርባን ለካህናት ካልሆነ ለተራው ምዕመን አይሰጥም ነበር። በምዕመናንና በካህናቱ መካከል ደግሞ እጅግ ሰፊ ልዩነት ነበር። ስለ ክርስቶስ ስለ መስቀሉ ስራ (ስለ ወንጌል) በቤ/ክርስቲያን ትምህርት አይሰጥም ነበር፤ በፈንታው ጳጳሳት መፅሀፍ ቅዱስን መሰረት ያላደረገ ፅሁፎችን በመፃፍ እነዚህም ትምህርቶች በመፅሀፍ ቅዱስ ፈንታ ካህናቱ ምዕመናንን እንዲያስተምሩ ያደርጋሉ። ኢየሱስም “…የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።” ማቴ16፥17-18 ይህን ክፍል መሰረት በማድረግ ክርስቶስ ለጴጥሮስ የመንግስተ ሰማያት መክፈቻ ቁልፍ ሰጠው፤ እርሱም የመጀመሪያው ጳጳስ ነበር።
ከዚያም ሲወርድ ሲዋረድ እየተሾሙ ላሉት ጳጳሳት ቁልፍ ተላልፎላቸዋል። ስለዚህም የመንግስተ ሰማያት ቁልፍ አለን፤ በመሆኑም ጳጳሳት አይሳሳቱም፣ የሚናገሩት የሚያስተምሩትም ሁሉ ትክክል ነው፣ አዲስና እንግዳ ነገር ቢያስተምሩም ምንም ጥያቄ ሳንጠይቅ ልክ እንደ እግዚአብሄር ቃል ልንቀበለው ይገባል፤ የሚል ብዙ የስህተት ትምህርቶች በቤ/ክርስቲያን ውስጥ ተንሰራፍቶ ነበር። በመንግስታት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ስለነበራቸው ነገስታቶች ይፈሯቸው፣ ይሰሟቸው፣ ይታዘዟቸውም ነበር።
መፅሀፍ ቅዱስ በላቲን ቋንቋ ስለነበር፣ ተራው ህዝብ መፅሀፍ ቅዱስ ማንበብ አይችልም ነበር። ላቲን ደግሞ የምሁራን ቋንቋ እንጂ የተራው ህዝብ ቋንቋ ስላልነበር፣ ተራው ህዝብ የሚሉትን ያለምንም ጥያቄ ተቀብሎ ይከተላቸው ነበር። ነገር ግን በየጊዜው የሚነሱ ምሁራኖች አንዳንዶቹ ምንም እንኳ ቤ/ክርስቲያን እንደሳተች ቢያውቁም ለጥቅማቸው፣ ለዝናቸው፣ ለክብራቸው በመሳሳት ተስማምተው መኖርን ይመርጣሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ በነፍሳቸው ተወራርደው አሻፈረኝ ከአመጽ ጋር ተስማምቼ በማመቻመች በፍጹም አልኖርም ብለው በመነሳታቸው ተሰደዱ፣ በእሳት ተቃጠሉ፣ ህያው ሳሉ ለአውሬ ተሰጡ፣ ተሰየፉ፣ በተለያየ አሰቃቂ አሟሟት ሞቱ። ዛሬ ከእነዚህ ሰማዕታት አንዱ ስለሆነው ጆን ኸስ (John Huss) ሰለተባለው ሰው ይዤላችሁ ቀርቤአለሁ።
ጆን ኸስ በ1380 ሁሲኔዝ በምትባል መንደር በፕሬግ (Prague) ቦሂሚያ (Bohemia) ማለትም የአሁኗ ቼክ ሪፐብሊክ (Czech Republic) ተወለደ። ወላጆቹም አቅማቸው በፈቀደላቸው በጊዜው ወደነበረው ምርጥ ወደተባለው የግል ትምህርት ቤት ልጃቸውን ላኩት። እርሱም ጎበዝና ታታሪ ስለነበር በዚያ የሚሰጠውን ትምህርት አጠናቅቆ ወደ ፕሬግ ዩኒቨርስቲ ተዘዋወረ። ከዚያም በከፍተኛ ማዕረግ ትምህርቱን አጠናቀቀ። ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ቤተልሄም ቤ/ክርስቲያን መጋቢ ሆኖ እያገለገለ በተጨማሪም በፕሬግ ዩኒቨርስቲ ያስተምር ነበር። ከዚያም በየደረጃው በፕሬግ ዩኒቨርስቲ የፋክልቲው ዲን በኋላም የዩኒቨርስቲው ፕሬዚደንት በመሆን አገልግሏል። በእነዚህም ጊዜያት እውነትን የሚገልጥ የአቋም ሰው፣ ከእውነት ጋር ቆሞ ዋጋ ለመክፈል የቆረጠ፣ በሚያየው በአካባቢው ክንዋኔዎችና ትዕይንቶች የሚመራ ሳይሆን በተረዳው እውነት የሚመላለስ ሰው ነበር። እውነት ሲገለጥ ደግሞ ከእውነት ጋር ያልቆሙ በጨለማ የሚመላለሱ ስራቸው ስለሚገለጥባቸው የእውነትን ብርሀን ይዘው የተነሱትን ለማጥፋት ይነሳሉ። ይህ ሰው በስብከቱም ሆነ በፅሁፎቹ ቤ/ክርስቲያን ያለችበትን መንፈሳዊ ምንዝርና፣ ካህናቶችና በጊዜው የነበሩ የቤ/ክርስቲያን መሪዎችን ስህተት ከመግለጥ ወደኋላ አላለም። ከዚህም የተነሳ በቤ/ክርስቲያን መሪዎች ከፍተኛ ጥላቻ አተረፈ። ይሁንና ትምህርቱ ተሰራጨ። በፕሬግና በአካባቢው ያሉ አንዳንዶቹ በትምህርቱ ተነክተው እውነተኛነቱንም ተረድተው በአንድ መስመር ከእርሱ ጋር አቋም ወስደው ለጌታ ተነሱ።
ከጆን ኸስ በፊት በእንግሊዝ አገር ጆን ክሊፍ (John Cliff) የተባለ የተሃድሶን ጮራ ያፈነጠቀ፣ የጳጳሳትን ስውር ስራቸውን፣ አይነ ስውራን ሆነው የአይነ ስውራን መሪ መሆናቸውን የገለጠ ሰው ነበር። እርሱም ለመጀመሪያ ጊዜ ጳጳሱ ፀረ ክርስቶስ ነው ብሎ የተናገረ ሰው ነው። በተጨማሪም ከላቲን ቋንቋ ወደ ፈረንሳይኛ ቋንቋ መፅሀፍ ቅዱስን ተርጉሟል። ትምህርቱም እስከ ቦሂሚያ ድረስ ደርሶ ተሰራጭቷል። በጆን ኸስና በብዙዎቹም ተቀባይነት አግኝቷል። በፕሬግ የነበረው አርክ ቢሾፕ የተሀድሶው እንቅስቃሴ በየጊዜው እያደገ መምጣቱ ስላሳሰበው እንቅስቃሴውን ለመግታት የጆን ክሊፍ ትምህርቶች ፈፅመው እንዳይሰጡ ፅሁፎቹም ተሰብስበው እንዲቃጠሉ የሚል ትዕዛዝን አስተላለፈ። ይሁንና ትዕዛዙ ያልጠበቀውን የተገላቢጦሽ ውጤትን አስከተለ። ተቃውሞውም እንቅስቃሴውን ይበልጥ አፋፋመው፤ አባላቱም በይበልጥ በግለት ተሞሉ፤ ፕሬግ ዩኒቨርስቲም በህብረት ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ትምህርቱን ለማስፋፋት ተነሳ። ጆን ኸስም በግልጥ የአርክ ቢሾፑን ትዕዛዝ መቃወሙን አሳወቀ።
ጳጳሱ ጉዳዩ ስላሳሰበው የክስ ደብዳቤ እንዲሰጣቸው በዚያም ደብዳቤ ሮም ፍርድ ቤት ቀርበው ጆን ኸስና ሌሎች ሶስት የዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰሮች ስለተከሰሱበት የሀሰት ትምህርት የመከላከያ ነጥቦቻቸውን እንዲያቀርቡ የሚል ነበር። ሶስቱ ፕሮፌሰሮች ሲቀርቡ ጳጳሱ ያነጣጠረውና ዋናው የእንቅስቃሴው መሪ ነው ብሎ ሊያገኘው የፈለገው ጆን ኸስን ነበር። ጆን ኸስ ግን የቦሂሚያው ንጉስና ንግስቲቱ እንዲሁም ልዑላልትና የዩኒቨርስቲውም አካል ጭምር ይወዱት ስለነበር፥ እዚያ ሄዶ ክፉ ነገር ይደርስበታል ብለው ስላሰቡ ከይቅርታ ጋር በእርሱ ምትክ ወኪል ልከናል ብለው ወደ ጳጳሱ ላኩ። ከዚያም ካርዲናል ኮሎና ጆን ኸስ ባለመቅረቡ አወገዘው። ጆን ኸስን ወክለው የቀረቡት ለጳጳሱ ይግባኝ ሲሉ ጳጳሱም ጉዳዩን እንዲያጤኑ አራት ካርዲናልን ሾመ። እነርሱም የመጀመሪያውን ውሳኔ አፀኑ። በተጨማሪም እርሱን ብቻ ሳይሆን ብዙ የእርሱን ሃሳብ ደጋፊዎች አወገዙአቸው። ይሁንና ከቤ/ክርስቲያን አውግዘው ቢያስወግዱትም እንቅስቃሴውን ሊገቱት አልቻሉም። ከዚያም በኋላ በተለያዩ ነጥቦች ላይ ብዙ ፅሁፎችን ፃፈ።
በ1414 ላይ በጳጳስነት ሹመት በተመለከተ በሶስት ሰዎች መካከል የነበረውን ክርክር እልባት ለመስጠት ሲል ኮንስታንስ ወደተባለው ወደ ጀርመን አገር የመላው የአብያተ ክርስቲያናት ስብሰባ ተጠራ። ነገር ግን የስብሰባው ስውር ዓላማ የተሃድሶ እንቅስቃሴውን ለመግታት ነበር። በዚህም ስብሰባ ላይ ጆን ኸስ እንዲቀርብና ጉዳዩን እንዲያቀርብ ጥሪ ደረሰው። ጥበቃ እንደሚደረግለት ከጀርመን ንጉስ ዋስትና ተሰጥቶት ጉዞ ጀመረ። በጉዞውም በየደረሰበት ቦታ ሞቅ ያለ አቀባበል ይደረግለት ነበር። በዚህም እጅግ እየተደነቀ ኮንስታንስ ከተማ ደረሰ። ጀርመን እንደደረሰ በታወቀ ጊዜ ወዲያውኑ ይዘውት በግዞት ቤት አኖሩት። ስቴፈን ፓሌዝ የተባለ ፕሬግ በሚገኙ ካህናት የተቀጠረና ሚካኤል ዴካሲስ የተባለ ከሮም ፍርድ ቤት ወኪል የሆነ ሁለቱ በጳጳሱ ፊት የጆን ኸስ ከሳሾች ሆነው ቀረቡ። የተከሰሰበትም የክስ አንቀጾች ተነበቡ፤ እነርሱም አርባ ሲሆኑ የተወሰዱትም በአብዛኛው ከፃፋቸው ፅሁፎች ነበር።
ጆን ኸስ ለተከሰሰበት ወንጀል ምላሽ እንዲሰጥ ተጠይቆ ምላሽ በመስጠት ላይ ሳለ ከጳጳሱ የሀጢዓት ይቅርት (ስርየት) ተቀብለሃልን ብለው ጠየቁት፡ እርሱም አልተቀበልኩም ሲል መለሰ። አቤቱታውን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ማቅረብ ተገቢ መሆኑን ወይም አለመሆኑን በተጠየቀ ጊዜ ደግሞ፥ ፍርድ ሲዛባ በቅንነት ያለ አድልዎ ለተጠቃውና ለተጨቆነው የሚፈርድ፣ የማይታለል የማያታልልም እንደ እርሱ ማነው ብሎ መለሰላቸው። ይህ ምላሽ የቤ/ክርስቲያን መሪዎች እንደመሆናቸው ሊያስደስታቸው ሲገባ ይልቁንም አበሳጫቸው። ወዲያውኑ በጉባኤው የክህነት ልብሱንና ቆቡን ገፈው በምትኩም “የሰይጣን ምስል” የተሳለበትና የሀሰተኛ ትምህርት ዋና መሪ የሚል ፅሁፍ የተፃፈበት የወረቀት ቆብ ደፉበት። እርሱም ጌታዩ ለእኔ ሲል የእሾህ አክሊል ደፍቷል፤ ለጌታዪ ከሆነ ታዲያ ይህማ ምንድነው አለ። ቢሾፑም ጆን ኸስ የተናገረውን ሰምቶ እንዳልሰማ በመሆን ነፍሱን ለዲያብሎስ አሳልፈን ሰጥተናል አለ። ጆን ኸስ ደግሞ ነፍሴን በደምህ የተቤዥሀት ጌታ ኢየሱስ ሆይ እኔ ግን ለአንተ አሳልፌ እሰጣለሁ አለ።
ጆን ኸስን በሰንሰለት አስረውት በህዝብ ፊት በእሳት ተቃጥሎ እንዲሞት ተፈረደበት። እንደችቦ የታሰረ ቅጠልና ጭራሮ ሰርተው እርሱን በመሀል አሰሩት። የከተማውም ከንቲባ የመጨረሻ እድል ልንሰጥህ እንወዳለን፤ ከዚህ በፊት ያስተማርከውንና የፃፍካቸውን ፅሁፎች ልትክዳቸው ፈቃደኛ ነህ ብሎ ጠየቀው፤ እርሱም ምላሽ ሲሰጥ እስከዛሬ በቃሌና በፅሁፌ ያስተማርኳቸው እውነት በመሆናቸው ይህን እውነት አሁን በደሜ ላትመው ወይም ላፀናው ተዘጋጅቻለሁ አለ። ሕያው ሳለ በእሳት አቃጠሉት። እሳቱም እየነደደ ሳለ የደስታና የድል ዝማሬን ይዘምር ነበር። ድምፁም እየደከመ መጣ።
በጆን ኸስና በመሰሎቹ ላይ ይደርስባቸው የነበረው ስደት የተሀድሶውን እንቅስቃሴ ይበልጥ እንደሰደድ እሳት አፋፋመው እንጂ አላዳፈነውም። የጆን ኸስ ሞት የብዙዎችን ዓይን አበራ፤ የጨለማውን ስልጣን ምስጢራዊ አሰራር፤ የጳጳሳትን የጥፋትና የክፋትን መንገድ ገለጠ፤ በአዲስ ሀይልና መሰጠት ለጌታ እንዲቆሙ አያሌዎችን አነሳሳ።
ወንጌል የቅብብሎች ሩጫ ውድድርን ይመስላል። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ከእኔ የተቀበልከውን የወንጌል አደራ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ ብሎታል። የወንጌልን አደራ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስና ለሌሎችም የወንጌልን ሩጫ ሮጦ አስተላለፈ፤ የወንጌልን አደራ ለማስተላለፍ ዋጋ ከፈለ፣ ተራበ፣ ተጠማ፣ በድንጋይ ተወገረ፣ እንደ ዕቃ በቅርጫት ውስጥ ገብቶ ተንገላታ፣ ፍርድ ቤት እንደ ወንጀለኛ ቀረበ፣ እስር ቤት ውስጥ ተጣለ፣ ኋላም በሰይፍ ስለት አንገቱ ተቆረጠ። ጢሞቴዎስ በኤፌሶን የመጀመሪያው ቢሾፕ ሆኖ ለብዙዎች የወንጌልን አደራ አስተላልፎ በአደባባይ በድንጋይ ተወግሮ በኤፌሶን ከተማ ተገደለ። ከላይ የተመለከትነው ጆን ኸስ በቃሉ ሰብኮ በአካል ሊደርሳቸው ያልቻለውን በፅሁፉ እውነትን ገልጦና ተርኮ ያመነውንና የኖረለትን እውነትና ሕይወት በደሙ አትሞ የወንጌልን አደራ ለተተኪው ትውልድ አስተላልፎ አለፈ።
ታዲያ ዛሬ ወንጌል ይህን የመሰለ ዋጋ ተከፍሎበት፥ አንቺ አንተና እኔ ጋር ደርሶ እንዴት ተቀበልነው? እንዴትስ ይዘነዋል? ወንጌሉ እየሮጠ ነው? ወይስ እኛ ጋር ደርሶ እኛ በራሳችን ነገር ተይዘን ቆሟል? ክርስትና ዋጋ ያስከፍላል፤ ወንድሜ እህቴ ከራሳችን ነገር እንውጣና በዚህ በቀረልን ዘመናችን የወንጌልን አደራ ይዘን ሩጫችንን እንሩጥ፤ በመጨረሻም እኛም እንደ ጳውሎስ ሩጫዪን ፈፅሜአለሁ ማለት እንችል ዘንድ።
ለዚህም ጌታ ይረዳናል! አሜን!
ወንድም ተስፋዪ ታደሰ