የቤ/ክርስቲያን መንፃት ለተሀድሶ

እኛ ያለንበት ይህ ዘመን መፅሀፍ ቅዱስ የመጨረሻው ዘመን ብሎ የሚጠራው ዘመን ለመሆኑ ብዙ ተጨባጭ ማስረጃዎችን ከምድራችን ሁኔታ ለመገንዘብ እንችላለን። በዚህ በመጨረሻው ዘመን ደግሞ እግዚአብሄር በቤ/ክርስቲያን በኩል ሊያደርገው የሚፈልገው ታላቅ ስራ አለ። ይህ ስራ በማቴ 24፥14 እንደተገለፀው የእግዚአብሄር መንግስት ወንጌል ለምድር ለአህዛብም ሁሉ እንዲሰበክ እንዲያዩት ምስክርም እንዲሆናቸው ነው። የመንግስት ወንጌል ብለን ስንል እስከዛሬ ከተነገረው ከምንሰማውም የመዳን ወንጌል ባሻገር የእግዚአብሄርን መንግስት ሉዓላዊነት፣ የእግዚአብሄርን ሁሉን አቀፍ ገዢነትና የበላይነት ብሎም ታላቅና ሃያል የመጀመሪያና የመጨረሻ አምላክነት እንዲሁም የጨለማ ስራ፣ የአሮጌው ስጋ ስራ፣ የወደቀውን ማንነት፣ የዲያብሎስንም ውድቀት ሽንፍትና ጥፋት በሀይል የሚነገርበት ወንጌል ነው። ይህ የእግዚአብሄር መንግስት አዋጅ ሊታይና ሊዳሰስ በሚችል እግዚአብሄራዊ (መጽሀፍ ቅዱሳዊ) መሰረትና አቋም ባለው ሕይወት በብልጫና በልቀት በመንፈስ ቅዱስም ሀይል የሚነገር ወንጌል ወይም አዋጅ ነው። ነገር ግን በቤ/ክርስቲያን ያለን ቅዱሳን ይህ የመንግስት ወንጌል የሚፈልግብንን የህይወት አቋምና ደረጃ ይዘናል? ቤ/ክርስቲያንስ ይህን አዋጅ ለማወጅ የምትችልበት ህዳሴና የብቃት ደርዝ ላይ ናት? አይደለችም። በዚህ ምክንያት እግዚአብሄር አስቀድሞ ቤቱን ማንፃት ይፈልጋል። መንፃት ደግሞ መታደስንና መታነፅን ያመጣል።

እግዚአብሄር ቤ/ክርስቲያንን ለማንፃት የፈለገባቸው አምስት ዋና ዋና ምክንያቶች ስንመለከት፥

በቤ/ክርስቲያን ያለውን ጨለማ ለማብራት

ጨለማ ቤ/ክርስቲያንን ቅርፅ የለሽና ባዶ የሚያደርጋት የመንፈሳዊ አይኖች እውርነት ማለት ነው።

ቅርፅ የለሽ ማለት ትርጉም የማይሰጥ፣ ውሱን የሆነ ባህሪ የሌለው /ያጣ/፣ ወጥ ያልሆነ ግንባታ ማለት ነው።

ባዶ ማለት ምንም ጥቅም የማይሰጥ፣ ልቀትና ብልጫ የሌለው ማለት ነው። /No meaning, No importance, No sense, No class, No excellency, No quality, value & worthy…/

እግዚአብሄር በቤ/ክርስቲያን ያለን ጨለማ በቃሉ እውቀት ሀይል ካላበራው ቤቱ መቆሸሹን ማየት አይቻልም። ቆሻሻውም ሳይፀዳ ይቆያል። ለምሳሌ በሉቃ 15፥8 ላይ እንደምንመለከተው የጠፋው ድሪም በቤት ውስጥ እያለ የጠፋ የመሰለው፥

1ኛ. ቤቱ ጨለማ ስለሆነ

2ኛ. ቤቱ ስለቆሸሸ

3ኛ. ፈላጊ ሳላላገኘ ነው።

ነገር ግን መብራት ሲበራ፣ ቆሻሻውም ሲጠረግ፣ ድሪሙንም አጥብቆ የሚፈልገው ሲገኝ ድሪሙ እዚያው ቤት ውስጥ ተገኘ። ስለዚህ በቤ/ክርስቲያን የጠፋ የመሰለው እግዚአብሄርን የመምሰል ህይወት ጨለማው በእግዚአብሄር ቃል ሀይል ሲገፈፍ ቆሻሻውም ሲጠራ ተፈልጎ የሚገኝና የሚገለጥ ይሆናል።

በኤፌ 5፥27 ላይ እንደምንመለከተው የቤ/ክርስቲያንን እርጅናና የፊቷን መጨማደድ ለማስወገድ እግዚአብሄር ቤቱን ሊያነፃ ይፈልጋል። ያረጀችንና የፊት መጨማደድ ያለባትን ቤ/ክርስቲያንን ማን ሊሰማት ይችላል? ማንስ ይወዳታል? እንዴትስ የመንግስቱን ወንጌል የመናገር ጥበብ ጉልበትና ሞገስ ይኖራታል? በዚህ ምክንያት አሮጌ ያደረጋትን የስጋ ስራና የዘልማድ አካሄድ ጥላ በእግዚአብሄር ፈቃድ የዘመኑን የእግዚአብሄርን ሃሳብ የምታስፈፅም እንድትሆን እግዚአብሄር ሊያነፃት ይፈልጋል።

በሮሜ 12፥1-2 ላይ እንደተፃፈው እግዚአብሄር ቤቱን በአይምሮ መታደስ ለመለወጥ ቤቱን ማንፃት ይፈልጋል። አይምሮው እንደ እግዚአብሄር ፈቃድና ሃሳብ በቃሉ ያልታደሰ ከእግዚአብሄር የሆነውን የትኛውንም ነገር መቀበል፣ ማስተላለፍ፣ መናገርና ማስረዳት አይችልም። ቤ/ክርስቲያን የእግዚአብሄር የሆነውን መቀበልና ማስተላለፍ እንድትችል በእይምሮ መታደስ ልትነፃ ግድ ነው።

እግዚአብሄር ቤቱን የሚያነፃበት አራተኛ ምክንያት ደግሞ ቤ/ክርስቲያን እንድታበራ ሌሎችም በጨለማ ያሉ ወደዚህ ብርሀን መምጣት እንዲችሉ ነው። ማቴ 5፥14-16 ቤ/ክርስቲያን ካላበራች በምድር ላይ ሁሉም ስለሚመሳሰል ፍጥረት ጨለማ መኖሩን እንዴት ማወቅ ይችላል? የሚያበራስ ከሌለ ብርሀን መኖሩን እንዴት ማየትና ማወቅ ይችላል?

እግዚአብሄር ቤቱን ሊያነፃበት የሚሻው አምስተኛው ምክንያት ቤ/ክርስቲያንን ካነፃት በኋላ ሊቀድሳት ስለሚፈልግ ነው። ኤፈ 5፥25-28 መቀደስ ማለት፥ መለየት፣ መብለጥ፣ መላቅ፣ እግዚአብሄርን መምሰል ማለት ነው። የተለየን፣ የላቀን፣ የሚበልጥን ሁሉም ሰው ይወደዋል፣ ሊያየውና ሊከተለውም ይፈልጋል።

እንግዲህ እግዚአብሄር ከላይ የተመለከትናቸውን አምስት የማንፃት ምክንያቶችና አሰራራቸውን በቤ/ክርስቲያን ለማድረግ ይፈልጋል፤ እያደረገም ነው። ነገር ግን ይህንን ደግሞ የእግዚአብሄርን የተሀድሶ ክንድ አጥብቆ መሻትና መፈለግ የቤ/ክርስቲያን (የቅዱሳን ሁሉ) ድርሻ ነው። መሻትና መፈለግ ደግሞ ራስን ለእግዚአብሄርን ቃል አሰራር ተገዢ ለማድረግ መዘጋጀትንና ከእግዚአብሄር ለመማር ለመለወጥ መወሰንን ይጠይቃል። ይህ ደግሞ እውን እንዲሆን በእግዚአብሄር ፊት በብዙ ፀሎትና ምልጃ መሆን ያስፈልጋል።

የቤ/ክርስቲያን ህዳሴ ከእያንዳንዳችን ህይወት ይጀምራል። የእያንዳንዳችን ህይወት እንደ ቃሉ ሲቃኝ እግዚአብሄርንም ወደመምሰል ህይወት ራሳችንን ስናስለምድ ሁልጊዜ በሁሉ እግዚአብሄርን የምናመሰግን ስንሆን እግዚአብሄር የሚወደውን ፈቃዱን በህይወታችን ያደርጋል። ያን ጊዜ ቤ/ክርስቲያን ወደ መንፃት ህይወት ትመጣለች፤ ስትነፃ እግዚአብሄር ይቀድሳታል።

ስለዚህ ቅድስት ቤ/ክርስቲያን የዘመኑን የእግዚአብሄርን መንግስት ወንጌል የምትናገር የመጨረሻዋ ዘመን ቤ/ክርስቲያን ናትና ይህችን ቤ/ክርስቲያን ተገልጣ ለማየት በፀሎትና በምልጃ እየተጋን ራሳችንን በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል እግዚአብሄርን ወደ መምሰል ህይወት እናሳድግ።

የእግዚአሄር ፍቅር የክርስቶስ ፀጋና ሰላም የመንፈስ ቅዱስም አንድነትና ህብረት ከሁላችን ጋር ይሁን። አሜን!

ሰላም ፀጋይ

Previous
Previous

ወንጌል ዋጋ ያስከፍላል 1

Next
Next

ለሞት እንዳልተኛ አይኖቼን አብራ