ለሞት እንዳልተኛ አይኖቼን አብራ

አለመታደስ አንድም መደምሰስ ነው። ድምሳሴው፣ በሰላ ምሳር ዛፍ ተቆርጦ ሲገነደስ አይነት የአፍታ መዓት ባይመስልም፣ ክፉ ደዌ ውስጥ ውስጡን እየበላው የሰራ አካላቱን ያሟሰሰው መጻጉዕ ተስለምልሞ ፀጥ እንደሚለው ዓይነት በለሆሳስ ነው።

ሰው ብቻውን የተተወ እንደሆነ ግስገሳው ወደ ውድመት ነው፤ ጥረቱ ሁሉ ይሟጠጣል፣ ማንነቱ ይሟጠጣል፣ አፈር አፈር ይሸተዋል። ራሱን በራሱ ማዳን የማይችል የሕይወት ውሃ ፈላጊ፣ የደረቅ መሬት እንቡጥ ነው። የመኖርና የመስራት ሰርቶም ውጤት የማምጣት አቅሙ ሕያው እግዚአብሄር ብቻ ነው። የሁልጊዜ ተደጋፊነታችን ምስጢሩም ይኸው ነው። እኛ ዘንድ ሕይወት አይመነጭም፣ እርሱ ዘንድ ግን ሕይወት አይቋረጥም።

“ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ፤ በእኔ የሚያምን፣ መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውሃ ምንጭ ከውስጡ ይፈልቃል።” ያለው፣ “በእርሱ ሕይወት ነበረች” የተባለለት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ለመሞት ብንፈልግ ይህን ያህል ብዙ መራቀቅ አይጠይቀንም፤ ሕይወት አለምላሚዎቹን ዋና ዋና ነገሮች፣ አየር፣ ውሃና ምግብ ላይ የምናሳየውን ያላሰለሰ ትጋት መቀነስና ማቋረጥ ብቻ ነው። በመንፈሳዊው አለምም ቢሆን ጉልበት የሚሻው ነገር ሕያውነት ነው። ለዚህ ነው ከሕያው አምላክ ጋር የሚደረገው ግንኙነት የክት ሳይሆን የወትሮ መሆን ያለበት። እየታደስን፣ እየለመለምን፣ አንገታችን ቀና የሚል ፍጡራን ነን። በተፈጥሮ አካሄድ ሲርበን ጉልበታችን እንደሚጥመለመል፣ ሲጠማን ምላሳችን ከትናጋችን እንደሚጣበቅ፣ ስንታፈን አየር ፍለጋ እንደምንወራጭ ሁሉ የውስጣዊ ሕይወት ተሃድሶ እንደሚያሻን ለማወቅም በቂ ምልክቶች አሉ።

ከብዙ በጥቂቱ እነሆ፡ ጸሎት፣ አምልኮና አገልግሎት አውቶማቲክ ይሆናል፤ በልቦና ታስቦ በውስጣዊ ጉጉት ተፈልጎ እያወቁ የሚያደርጉት ሳይሆን ቁልፉ ሲነካ እንደሚሽከረከር የግዱን በዘልማዳዊ ህግ ይከናወናል፤ ስለዚህም ይታክታል ፍችውም ይደበዝዛል። የባሰም እንደሆነ ከናካቴው ይቀራል።

መኖር ማለት የየዕለቱን ጉሮሮ የመድፈን ተግባር ለማከናወን የሚደረግ አድካሚ አዙሪት ብቻ ይሆናል። ይኸው የኑሮ ገበያ ቱማታና የስጋ ፍላጎት ከበሮ ድምድምታ በእውቀትም በደመነፍስም የምንከተለው ዜማ ምት ይሆናል። “አዳሜው ሁሉ የሚሮጥለት እንዲያውም ሌላ መሮጫ ምክንያት ባይኖር ነው።”

በክፉና በደግ፣ በንጹህና በርኩስ፣ በጥበብና በጅልነት፣ በእግዚአብሄር መልአክና በጋኔን፣ በእውነትና በሃሰት መሀከል ያለው የልዩነት መስመር እየወየበ ከአንዱ ወደ ሌላው ዘው እያሉ መመለስ እንዲያም ድንበሩን የሽርሽር መስክ ማድረግ እየተለመደ ይመጣል።

“ለካ ልቤን ንፁህ ያደረኩት በከንቱ ነው፤ እጄንም በየዋህነት የታጠብኩት በከንቱ ኖሮአል!” የሚል ውስጣዊ ማልጎምጎም እየበረታ ይመጣል።

ከሰዎች ጋር በተለይ ደግሞ ቅርብ ከሆኑት ወንድሞቻችን እህቶቻችን ጋር ያለን ፍቅራዊ ትኩሳት እየበረደ ይመጣል። ቢኖሩም ባይኖሩም አብረን ብንሆንም ባንሆንም ደንታ ቢስ እየሆንን ስንቀጥል አልፎ አልፎ እንዲያውም አጠገባችን ባይሆኑ እንመርጣለን። ክርስቲያናዊ ህብረት ይጎፈንነናል፤ “እስቲ ተውኝ” የስልቹነታችን ዜማ ይሆናል።

በምንኖርበት አካባቢ ከአፈር ከቅጠሉ ጋር ተዋህደን ቀለማችን ሳይለይ ብንረሳ እንመርጣለን። ለውጥ የማምጣት ፍላጎታችን ይነቅዛል፤ የማይለማ የማይሰማ ዱልዱም መሆን ጣጣ የሌለበት ሕይወት ይመስለናል።

በአፋችን “እሰይ በሰማይ ቤት አለኝ” እያልን እየዘመርን በልባችን “እስቲ እዚህ ያለውን ቤት ባሳመረልኝ” እንላለን። ያኛው ሩቅ የማይደረስበት ምናልባት ስለርሱ ማሰብ ጅል የሚያድርግ እንደሆነ የሚቆጠር፣ ተጨባጩን ቁሳዊ ዓለምን ግን በትኩስ ስግብግብነት የሚያፈቅር አውሬ ልብ ይረባብናል።

ተሐድሶ ማለት ከዘልማድ እስር ቤት፣ ከሞት እስራት በመንፈስ ቅዱስ ሃይል ተመንጥቆ መውጣት ነው፤ ሰባት ጊዜ ከተነጠረ ብር ይልቅ በጠራው በእግዚአብሄር ቃል እንጀራ መበርታት ነው። በእግዚአብሄር ደስታና እርካታ ማግኘት ነው፤ በወገኖች ፍቅር መለምለም ነው፤ በፅድቅ ሕይወት እርምጃ የሚገኝ አንበሳዊ ድፍረት ነው፤ በተልዕኮ እርግጥኝነት ምክንያት የሚደረግ ግሥገሳ ነው። ተሐድሶ የቦዘ ዓይን ፍንትው የሚልበት፣ ከሁለንታለም ፈጣሪ ጋር ፍቅር የሚያገረሽበት፣ እንቅስቃሴ ሁሉ ትርጉም የሚያገኝበት ደማቅ ኑሮ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጅም ወታደርም የመሆን ብቃት ነው።

ይህ ሁሉ እንዴት ሊሆን ይችላል?

ከሁሉ በፊትና በላይ ልዑል እግዚአብሄር አዳሽ አምላክ ነው። በፈጣሪነቱ የሚታወቀው ይህ አምላክ፣ በአዳሽነቱም ወደር የለውም። የደረቁ አጥንቶችን ተንቀሳቃሽ ሠራዊት ለማድረግ አራት ነፋሳት የሚጠራ፣ መቃብር ከፋች ብርቱ ጌታ ነው። ያሁን ዘመን ዋናው ስራው ሙታንን መቀስቀስ ነው።

በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል የግንኙነት እድሳት፣ በቅዱስ መንፈሱ በኩል የንጽህናና የሀይል እድሳት እያደረገ ነው።

መንገዱ የተወላከፈ እንግድግድ የሰው ልጅ የሞት ሽረቱን መንከላወስ ትቶ ለምርመራ መቆም አለበት።

“እንግዲህ ከወዴት እንደወደክ አስብ፣ ንስሀም ግባ፣ የቀደመውንም ስራህን አድርግ” የተባለው በብዙ መስመር ብርቱ የነበረው ፍቅሩ ግን ያረጀበት የቤ/ክርስቲያን መሪና ህዝቡ ናቸው።

እስኪ ነገሮችን ላይ ላይ የመነካካት ግልብነታችንን ትተን ስለሕይወታችን አምርረን እናስብ፤ “አስብ” ተብለናላ! እስኪ ጎምዛዛውን ፍሬ ከአፋችን እንትፋው፣ መንፈሳዊ ጭካኔ እንልመድ። “ንስሀ ግባ” ማለት ሌላ ምንድን ነው? እስኪ ደግሞ በመፅሀፉም በልምድም የምናውቀውን ተገቢ ስራ እንደገና እንቀጥል፤ “የቀደመውን ስራህን አድርግ” ማለቱ ቋሚ የኑሮ መልክ ያለ መሆኑን ያመለክታል።

በፍቅረ እግዚአብሄር በፍቅረ ሰብዕ እንታደስ

በእውነት ትምህርት በንፁህ ሃይማኖት እንታደስ

በሰላም ናፍቆት በእርቅ አስተናጋጅነት እንታደስ

በቅዱስ ኑሮ በቅዱስ ሃሳብ እንታደስ

መንፈስ ቅዱስ ለእኔና ለወገኖቼ አዲስ ነፋስ ላክልን፣ ሕያውነት ወደ አጥንቶቻችን ውስጥ ይዝለቅ፣ የምድሪቱም ገጽ ይፍካ።

ንጉሴ ቡልቻ

ከብርሃን መጽሔት ቁጥር 58 - 2000 ዓ.ም. የተወሰደ

Previous
Previous

የቤ/ክርስቲያን መንፃት ለተሀድሶ

Next
Next

በሆዱ ይሰድበኛል?