ካንተ ወዴት ይሸሻል?

ኧረ ካንተ የት ይሸሻል?

ሁሉን ነገር አይንህ ያያል፣

እጅህ ከዚህ እስከዚያ ጥግ ይዘረጋል።

በመርከቧ ስውር ክፍል?

በባህሩ ጥልቅ ወለል?

ወይስ ካውሬው ሆድ እቃ ውስጥ?

በሚያሳቅቅ የፍርሃት ማጥ።

ከቶ ራሴን በምን ዘዴ ልደብቀው?

አሳፋሪው ማንነቴን እንዳታየው።

ባነበብኩት በዕውቀቴ?

ባንደበተ ርቱነቴ?

በሸንጋዮች የፍቅር ውል?

በማያውቁኝ ያድናቆት ቃል?

በታይታው ማንነቴ?

አስመስዬ በቀረፅኩት እኔነቴ?

ደስታ ባልወለደው ፈገግታዬ?

ሃዘን በሌለው እምባዬ?

ድምጽ ብቻ በሆነ እሪታ?

ፀፀት በሌለው ይቅርታ?

አቅም በሌለው ፉከራ?

በዘር በአጥንት ቆጠራ?

ከቶ ራሴን እምን ስፍራ ልደብቀው?

አሳፋሪው ማንነቴን እንዳታየው።

ገፅ 3 አቤንኤዘር ወንጌላዊት ቤ/ክርስቲያን

ካንተ ወዴት ይሸሻል?

ልግባ ይሆን እጎተራው?

የእህል አይነት ከሞላው፣

ልሂድ ይሆን ወደማሳው?

አይንህ ማርኰት ልምላሜው- ችላ ብለህ ታልፈኝ እንደሁ።

ወይ ከሳጥኔ ውስጥ ልግባ?

ባይሆን ስደርብ ውድ ካባ፣

ለክብርና ለሞገሴ ተሽቀርቅረህ፣

እንዳታየኝ አቀርቅረህ።

ከቶ ራሴን በምን ዘዴ ልደብቀው?

አሳፋሪ ማንነቴን እንዳታየው።

ፍጥረትማ፤

ፍጥረማ ውጪን አይቶ

ባየው ብቻም ተመስርቶ ይበይናል፤

ክፉ ስምን ለመለጠፍ፣

ዘንባባንም ለማነጠፍ ይቸኩላል።

አንተ ግን- አንተ ግን ዘልቀህ ታያለህ፣

አብጠርጥረህ ትለያለህ።

ከጓዳዬ መዝጊያ ጀርባ ብሸሸግም፣

አንተ ከቶ እይታህን አትስትም።

መጋረጃ ብጋርድህ፣

አንተ አሁንም ታየኛለህ።

ብከናነብ ብርድ ልብሴን፣

አላገደህ ማየት እኔን።

ባንሾካሹክ ትሰማለህ፤

ብሸሸግም ታየኛለህ፤

ብሮጥ እንኳን አላመልጥህ፤

ግዙፍ ብሆን አላስፈራህ።

ዴት ይሸሻል?

ገፅ 4 አቤንኤዘር ወንጌላዊት ቤ/ክርስቲያን

ኧረ ካንተ የት ይሸሻል?

ሁሉን ነገር አይንህ ያያል፤

እጅህ ከዚህ እስከዚያ ጥግ ይዘረጋል።

ፍጥረት እንኳ - ፍጥረት እንኳ ውጪን አይቶ፣

ባየው ብቻም ተመስርቶ፣

ያሞግሳል፤ ያጣጥላል፤

ከፍና ዝቅ እያረገ ይበይናል።

ክፉ ስምን ለመለጠፍ፣

የሞት አዋጅ ለመለፈፍ፣

ዘንባባንም ለማነጠፍ፣

ባድናቆትም ለማንሳፈፍ፣

ይቸኩላል፤ ይሯሯጣል፤

ያንተ አይን ግን ዘልቆ ያያል።

እንዲያው ሁሉን ለመጠቅለል፣

የምወደው ዘማሪ እንዲል፣

ካንተ ካንተ ካንተ ምን ይደበቃል?

ፍጥረት እርቃኑን ነው ግልጥልጥ ብሏል።

ግዮን

ሰኔ 2001 (በዘማሪ ደረጀ ከበደ “ካንተ ምን ይደበቃል” በሚለው ዝማሬ መነሻነት የተጻፈ)

Previous
Previous

በሆዱ ይሰድበኛል?

Next
Next

አንደበት እሳት ነው!