ስለምን አንለወጥም?

በዚህ ዘመን ያለን ክርስቲያኖች ሕይወታችን እግዚአብሄርን የሚያስደስት እንዲሆን ከተፈለገ፥ መሰረታዊ በሆኑ ቃሎቹ መነካት እና መዳሰስ አለበት። እኛ ግን ነገሮችን የምንለካው ለጌታ አድርገነዋል ከምንለው ስራዎች መካከል ከጥቂት ነጠላ ሰረዝ ሁኔታዎች ጋር በማቀናጀት እና ለዛም ደግሞ ስፋትና ጥልቀት በተያያዘ መልኩ በመግለፅ ላይ ነው። እግዚአብሄር አምላካችን ግን እንደምናስበውና እንደምንገምተው ሳይሆን የልጁን የኢየሱስን ፍፁም እና ቅዱስነት በማየት ለነገሮቻችን ሁሉ እልባትን ይሰጠናል። ምክንያቱም በሰማይ እና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው። እንግዲህ ይህ የእግዚአብሄር ምርጥ ሐሳብ ነው። እኛንም በዚህ ምርጥ እና ቅዱስ ሐሳቡ በኢየሱስ ክርስቶስ ይጠቀልላል ብዪ አምናለሁ።

ስላለንበት የመንፈሳዊ ህይወት ስለምን አንለወጥም ብዬ አስባለሁ። ምክንያቶቹስ ምንድን ናቸው እያልኩ አወጣለሁ አወርዳለሁ። ምክንያቶቹም ብዙ ቢሆኑም ግን፥ የግል ሕይወታችን ከእግዚአብሄር ሐሳብ እና ፈቃድ ጋር ባለመቀናጀቱ የመጡ መሆናቸውን በጥቂት ላሳስብ እወዳለሁ። በአሁኑ ጊዜ ያለን ክርስቲያኖች ሕይወቴን እንዴት አድርጌ ልምራ፣ እንዴት አድርጌ የእግዚአብሄርን ቃል ላጥና፣ እንዴት አድርጌ ልለወጥ የሚሉት ችግሮች እንደሌሉብን የምናውቀው ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ታማኝ በሆኑ አገልጋዮች ትምህርቶችና ስብከቶች መፅናናትና መበረታታ እናገኛለን። አልፎ ተርፎም የመዝሙር ካሴቶች፣ መፅሔቶች፣ መፅሐፍቶች፣ የክርስቲያን ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች እንዲሁም በየጊዜው የሚደረጉ ኮንፍራንሶች በዙሪያችን ከመጠን በላይ አሉ። ሆኖም ግን ይህ ሁሉ ሆኖ አለመለወጣችን እና ጌታን አለመምሰላችን ለምን ይሆን? ምናልባት አላስተዋልነው ይሆናል እንጂ ብዙዎቻችን በሁለት አለም ላይ መኖር ከጀመርን ቆይተናል። እምነታችንን እና እንቅስቃሴአችንን ለሁለት በመክፈል በቤ/ክርስቲያን ባሉ ሰዎች እና በምድራዊያን ሰዎች መካከል የምንኖረውን አኗኗር በመለዋወጥ እንደ አካባቢው ሁኔታና እንደጊዜው በሚሉት አጉል ጥበብ ተጠምደናል። ጌታ እኔን ምሰሉ እያለ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም እያለ እኛ ግን እነዚህ ምርጥ ቃሎቹ ካረጁብን እና እነዚህንም ቃሎች የሚጠብቁ ክርስቲያኖች ሞኝ መስለው ከታዩን ውለን አድረናል።

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ አለማዊ ኑሮአችንን ማለትም ምድራዊ ህይወታችንን ለማሳካት አልፎም ከሌሎች ለመብለጥና የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ከአስፈላጊው በላይ በመስራት በገንዘብ ማግኛ ሂደቶች ተጠምደናል። ያም ሆኖ ግን በዚህ ሁሉ ውስጥ አለመርካት ይታይብናል። እግዚአብሄር አምላክ ለእኔ ጊዜ ስጡ፣ ለቃሌና ለፀሎት ጊዜ ስጡ እያለ እየተናገረ፥ ንግግሮቹንና አባባሎቹን ችላ ካልን ቆይተናል።

በክርስትና ሕይወታችን እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት አለሞች የሰማይና የምድር ያህል አራርቀን መያዝ ሲገባን፣ አዛምዶ በግዴለሽነት ለመያዝ በምናደርገው ጥረት ውስጥ ምድራዊነቱ በልጦብን ሕይወታችንን በቁጥጥር ውስጥ ካደረገ ሰንብቶአል። የምናምነው ነገር እና የምንኖረው ኑሮ ተጋጭቶብናል። በየስብሰባውና በየኮንፍራንሱ የጌታ ቃል መጣልን ተገለጠልን እያልን እናጨበጭባለን። (እልል እንላለን) ሆኖም ግን በሰማነውና ባደነቅነው ነገር ስንኖር አንታይም።

ብዙዎቻችን የደቀመዝሙርን ሕይወት ሳንኖር ድንቅና ተአምራት እንዲገለጥ እንፈልጋለን። ብሎም ለእግዚአብሄር ራስን ስለመስጠት፣ ስለ ቅድስና፣ ስለፀሎት፣ እግዚአብሄርን ስለመፍራት፣ ስለፍቅር፣ ስለታማኝነት፣ ስለ ቃሉ መገለጦች እናወራለን። ሆኖም ግን በሕይወታችን ላይ ሲገለጥ እና ሲሰራ አይታይም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በነበረበት ዘመንም የነበሩ ሰዎች እንደኛው የቁሳዊ ነገሮች ተገዢ እንደነበሩና ግላዊነት እንደነበራቸው ከወንጌላት ለማወቅ ይቻላል። ቢሆንም ግን ጌታችን ኢየሱስ ለውጥ ስለሚያስገኙት ትምህርቶች ሲናገር እንዲህ ብሏል “ጠላቶቻችሁን፣ ውደዱ፣ ለሚጠሏችሁ መልካም አድርጉ፣ ስለሚያሳድዷችሁ ፀልዪ፤ ከእናንተ መካከል ጌታ ለመሆን የሚፈልግ ባሪያ ይሁን፤ በምድር ላይ ሃብት አትሰብስቡ፤ ሰው ያለውን ሁሉ ካልተወ ደቀመዝሙሬ ሊሆን አይችልም።” የሚሉአቸው ትምህርቶቹ ጥቂቶቹ ናቸው። እነዚህ ቃሎች በሕይወታችን ላይ ትልቅ ስፍራ ሊሰጣቸው የሚገቡ ናቸው። ሕይወታችንን በክቡር ደሙ ገዝቶታል፤ እና ሐዋርያው ጳውሎስ ሲናገር በዋጋ ተገዝታችኋል እና የራሳችሁ አይደላችሁም። ስለዚህ ነፍሳችንን በሚያከሳና በሚያጎሳቁል በዚህ አለም ቁሳቁሳዊና የሀብት አስተሳሰብ መሰነካከል የለብንም። ጌታችን የጊዜአችን፣ የገንዘባችን፣ የእኛነታችን እና የሚኖረን ነገር ሁሉ ጌታ እንዲሆን አስፈላጊውን ሁሉ ልናደርግ ይገባናል። ሐዋርያው በ1ኛ የዮሐንስ መልዕክቱ 2፥6 ላይ ሲናገር “በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ (ክርስቶስ) እንደተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል” ይለናል። ክርስቶስ ባለበት ሕይወት ሁሉ ፍቅር እና መለወጥ አለ፤ እሱ በእኛ እንዲኖር እንፍቀድለት።

ቃሎቹን ለመፈፀም ጌታ በፀጋው ያግዘን!

ኤልያስ

ከሳክራሜንቶ

Next
Next

እቀብተ-እምነት (Apologetics)